Friday, November 22, 2024
spot_img

የኤርትራ መንግሥት ወታደሮቹ በትግራይ ክልል የሰብአዊ አቅርቦት አስተጓጉለዋል መባሉን ወድቅ አደረገ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ሰኔ 10፣ 2013 ― የጎረቤት አገር ኤርትራ መንግሥት በትግራይ ክልል የሚገኙ ወታደሮቹ የሰብአዊ አቅርቦት እንዲስተጓጎል አድርገዋል መባሉን እንዲሁም እርዳታን እንደ ጦር መሳሪያ ተጠቅሟል በሚል የቀረበበትን ክስ ውድቅ አድርጎታል፡፡

ይህንኑ በመንግሥታቱ ድርጅት የኤርትራ ቋሚ መልእክተኛ አምባሳደር ሶፊያ ተስፋማርያም በጻፉት ደብዳቤ ገልጸዋል፡፡

አምባሳደር ሶፊያ ደብዳቤውን የጻፉት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ኃላፊ ማርክ ሎውኮከ፣ የዓለም ምግብ ድርጅት ዳይሬክተር ዴቪድ ቢያስሊ እና ሌሎችም አካሄደውታል በተባለ የትግራይ ክልልን ሰብአዊ ሁኔታ የሚመለከት መደበኛ ያልሆነ ውይይት ላይ የኤርትራ ወታደሮቹ በክልሉ ሰብአዊ አቅርቦት አስተጓለዋል በሚል ተነስቷል በሚል ነው፡፡

ቋሚ መልእክተኛዋ በደብዳቤያቸው አገራቸው በትግራይ ክልል የአብአዊ አቅርቦት እንዳይዳረስ እንቅፋት ሆና አታውቅም ያሉ ሲሆን፣ እርዳታን እንደ ጦር መሳሪያ ተጠቅማለች መባሉም እንኳን አሁን ቀርቶ ከ20 ዓመት በፊት ከኢትዮጵያ ጋር በገባችበት ጦርነትም ጭምር እንዲህ ዐይነት ተግባር አልፈጸምንም ብለዋል፡፡

በዚሁ ደብዳቤ አምባሳደር ሶፊያ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ኃላፊ የሆኑት ማርክ ሎውኮክን በትግራይ ክልል ጦርነት ብቸኛው ተጠያቂ ነው ላሉት ሕወሃት በመሟገት ተጠምደዋል ሲሉም ወቅሰዋል፡፡

በተጨማሪም የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የተሳሳተ መረጃ እየረጨ በኤርትራ ላይ ዘመቻ ከፍቷል በማለትም ቅሬታቸውን ሰንዝረውበታል፡፡

በመንግሥታቱ ድርጅት የኤርትራ ቋሚ መልእክተኛ አምባሳደር ሶፊያ ተስፋማርያም በደብዳቤያቸው ማሳረጊያ፣ አገራቸው በሕወሃት ተፈጽሟል ያሉትን ከባባድ ወንጀሎች ለማቅለል የሚደረጉ ዘመቻዎን እንዲሁም ዓለም አቀፍ ሕግጋትን በመጣስ የአገራትን ሉአላዊነት ተላልፎ የሚደረጉ ተግባራትን እንደማትቀበል አሳውቀዋል፡፡

የኤርትራ ቋሚ መልክእክተኛ አላግባብ ተወቅሰዋል ያሏቸው በኢትዮጵያ መሬት ላይ የሚገኙ የኤርትራ ወታደሮች፣ በትግራይ ክልል የተለያዩ አሰቃቂ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በመፈጸም በተለያዩ አካላት ሲወቀሱ የሰነበቱ መሆናቸው ይታወሳል፡፡

በጥቅምት ወር በትግራይ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ ወደ ኢትዮጵያ መሬት የዘለቁት ወታደሮቹ፣ የኢትዮጵያን መሬት ለቀው ይወጣሉ ተብሎ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከተነገረ አስር ሳምንት ያለፈ ቢሆንም፣ አሁንም ድረስ በትግራይ ክልል እንደሚገኙ ይነገራል፡፡

ወታደሮቹን አስመልክቶ በትላንትናው እለት የተናገሩት በተመድ የኢትዮጵያ ቋሚ መልእክተኛ ታዬ አጽቀሥላሴ፣ የሚቀሩ አንዳንድ ቴክኒካዊ ጉዳዮች ተጠናቀው በቅርቡ በርግጠኝነት ከኢትዮጵያ ይወጣሉ ማለታቸውን አሶሽየትድ ፕረስ ዘግቦ ነበር፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img