Sunday, September 22, 2024
spot_img

በሳዑዲ ዐረቢያ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን በጸጥታ ኃይሎች እየተንገላቱ መሆኑን ተናገሩ

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ሰኔ 9፣ 2013 ― ኢትዮጵያዊያኑ በአገሪቱ መንግሥት የፀጥታ ኃይላትና ነዋሪዎች ከፍተኛ ወከባ፣ እስር እና ዝርፊያ እየደረሰባቸው መሆኑ ተናግረዋል፡፡

የጸጥታ ኃይሎቹ በአገሩ የሚገኙ የመኖሪያ ፈቃድ ያላቸውንም የሌላቸውን ኢትዮጵያውያን ቤቶች እየዘረፉ ለእስር በመዳረግ ላይ መሆናቸውን የችግሩ ሰለባ ኢትዮጵያውያን ለዶቼ ቨለ ተናግረዋል፡፡

ቃላቸውን ከሰጡ ነዋሪዎች መካከል ለ8 ዓመት ያህል ጅዳ ነዋሪ እንደሆኑ የገለፁ ኢትዮጵያዊ የመኖሪያ ፈቃድ እንዳላቸው እየተናገሩ ከባለቤታቸው እና ሁለት ልጆቻቸው ጋር ለ3 ቀን ታስረው መፈታታቸውን ገልጸዋል። እንደ ግለሰቡ ከሆነ የፀጥታ ኃይሎቹ በሩን ሰብረው ሲገቡ ‹‹ኢቃማ [ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ] አለን እያልናቸው እንኳን ሊሰሙን አልቻሉም›› ብለዋል፡፡

ባለፉት ሁለት ቀናትም የጸጥታ ኃይላቱ ‹‹ሐበሻ›› የሚሏቸውን ኢትዮጵያውያን ማሰርና ቤቶቻቸውን መስበር መቀጠላቸውን ነዋሪዎች አመልክተዋል።

ሳዑዲ ዓረቢያ ጅዳ በሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽ/ቤት ምክትል ቆንስል ጄኔራል አቶ ነቢዩ ተድላ በበኩላቸው የቆንስላው የሳዑዲ ዓረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኃላፊዎች ስለእስሩ እንዲያብራሩላቸው ትናንት መነጋገራቸውን ጠቅሰዋል።

ኃላፊዎቹ የተለመደ የሳዑዲ ሕገ ወጦችን የመለየት ሥራ እንደሆነ እንደተናገሩ እና በመሀል ሕጋዊ ነዋሪዎች እንግልት እየደረሰባቸው መሆኑን ቆንስላው ማስረዳቱን ተናግረዋል።

አቶ ነቢዩ ‹‹መንገለታታት እንደዚሁም ቤቶቻቸው ውስጥ የሳዑዲ ወታደሮች ገብተው ፍተሻ የማድረግ አይነት ነገሮች እንደደረሰባቸው ጠቅሰንላቸው፤ ይሄ ጉዳይ እንዲቆም እንደ ቆንስላ ጽ/ቤት ጠይቀናል።

ይህን ጉዳይ ለሚመለከተው የሳዑዲ የፖሊስ እና የደኅንነት ተቋማት እንደሚያቀርቡ ቃል ገብተውልናል›› ብለዋል።

ቆንስላ ጽ/ቤቱ በጅዳና መካ፣ ጂዛን፣ መዲናና አባሃ ከተሞች እስካሁን ድረስ ከሰባት መቶ በላይ የታሰሩ ኢትዮጵያውያንን ማስፈታታቱንም ተናግረዋል።

የቆንስላ ጽ/ቤቱ የሳዑዲ የፀጥታ አስከባሪ አካላት በሳዑዲ የተለያዩ ከተሞች ላይ የመኖርያ ፈቃድ ባላቸውም ይሁን በሌላቸው ነዋሪዎች ላይ የፍተሻና የአፈሳ ርምጃ እየወሰዱ እንደሆነና ዜጎች ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መልዕክት ማሠራጨቱ አይዘነጋም።

የፎቶ ምንጭ፡ ኢንተርኔት

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img