Wednesday, October 9, 2024
spot_img

ካናዳ በትግራይ የተፈጸሙ ወንጀሎች ላይ ለሚካሄደው ምርመራ የገንዘብ ድጋፍ አደርጋለሁ አለች

አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ሰኔ 8፣ 2013 ― የካናዳ መንግሥት በትግራይ የተፈጸሙ ወንጀሎች ላይ ለሚካሄደው ምርመራ የገንዘብ ድጋፍ አደርጋለሁ ማለቷ ተሰምቷል፡፡

አገሪቱ 600 ሺሕ ዶላር እደግፈዋለሁ ያለችው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ቢሮ እና በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ጥምረት በክልሉ በጦርነቱ ተሳታፊዎች ደርሷል የተባለውን የወንጀል ምርመራ ነው፡፡

በጉዳዩ ላይ የተናገሩት የካናዳ የውጭ ጉዳዮች ክፍል ቃል አቀባይ ፓትሪሲያ ስኪነር፣ ምርመራው ግልጽ እና በገለልተኛነት መደረግ ያለበት መሆኑን በመጠቆም፣ በወንጀል ተሳትፎ እንዳላቸው የሚረጋገጥ አካላትም ተጠያቂ እንዲደረጉ ጠይቀዋል፡፡

ቃል አቀባይዋ አክለውም አገራቸው ካናዳ አሁንም ቢሆን በትግራይ ክልል ተፈጽመዋል የሚባሉ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እጅጉን እንደሚያሳስባቸውም ገልጸዋል መባሉን ግሎብ ኤንድ ሜይል ዘግቧል፡፡

ሆኖም የዜና ተቋሙ ልክ እንደ አሜሪካ ሁሉ ካናዳም በኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ላይ ወደ ማእቀብ መጣል ልታመራ እንደምትችል ጠይቄ፣ ቃል አቀባይዋ የካናዳ መንግሥት የማእቀብን ጉዳይ አቅልሎ እንደማይመለከተው በመንገር፣ አስፈላጊ ሲሆን ግን እንደምትጠቀምበት ጥቆማ ሰጥተዋል ነው ያለው፡፡

ባለፈው ወር የአሜሪካ መንግሥት በትግራይ ክልል ተከስቷል ላለው ጉዳይ ተሳትፎ አላቸው በሚል የፌዴራል መንግሥት፣ የሕወሃት መሪዎች እና የኤርትራ ባለሥልጣናት ላይ የቪዛ ማዕቀብ መጣሉ አይዘነጋም፡፡

የማእቀቡን የጣለው ባይደን አስተዳደር በባለስልጣናቱ ላይ የጣለውን ማእቀብ ሌሎች አገራትም እንዲቀላቀሉትም ጥሪ ማድረጉ አይዘነጋም፡፡

ይህንኑ የቪዛ ማእቀብ ለማስነሳት የኢትዮጵያ መንግሥት ትላንት ምሽት በአንጋፋው ዲፕሎማት ተቀዳ ዓለሙ የተመራ ልኡክ ወደ ዋሺንግተን ማቅናቱም ተነግሯል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img