Sunday, September 22, 2024
spot_img

ምርጫ ቦርድ ከዚህ በኋላ ምርጫው እንደማይራዘም አስታወቀ

እንዲጠቀሙበት ተጠየቀ አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ሰኔ 3፣ 2013 ― የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሊካሄድ አስር ቀናት ብቻ የቀሩትን ስድስተኛውን አገራዊ በቀኑ እንደሚደርግና ከዚህ በኋላ እንደማይራዘም አስታውቋል፡፡

ቦርዱ ይህን ያሳወቀው ለስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ካሳተማቸው የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ውስጥ ለ54 የምርጫ ክልሎች የታተሙ የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ችግር እንደነበረባቸው በገለጸበት ማብራሪያው ነው፡፡

የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ትላንት ረቡዕ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ከድምጽ መስጫ መረቀቶች ጋር በተያያዘ ቦርዱ ያጋጠመውን ችግር ያስረዱ ሲሆን፣ ከችግሮቹ መካከል ራሳቸውን ከምርጫው ያገለሉ ዕጩዎች በድምጽ መስጫ ወረቀቶች ላይ ታትመው መገኘታቸውን ሲስረዱ፣ በዕጩነት የተመዘገቡ ተወዳዳሪዎች ያልተካተቱባቸው የታተሙ የድምጽ መስጫ ወረቀቶችም ቦርዱ ከመረጃ ቋቱ ጋር ባደረገው የማመሳከር ሂደት ወቅት መገኘታቸውን አስረድተዋል። በፓርቲዎች የተቀየሩ ዕጩዎች በታተሙ የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ላይ ሰፍረው መገኘታቸውንም እንዲሁ ሰብሳቢዋ በችግርነት አንስተዋል።

ምርጫ ቦርድ በጽምጽ መስጫ ወረቀቶቹ ላይ ችግር እንዳለባቸው ያወቀው ከሦስት ቀን በፊት ግንቦት 30 ባካሄደው የሰነድ ማመሳከር እንደሆነ የቦርዱ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ሶልያና ሽመልስ እንደነገሩት ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ዘግቧል፡፡

ቦርዱ ትላንት ማምሻውን ባወጣው የምርጫ ክልሎች ዝርዝር መሰረት፤ የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ህትመት ችግር ያልተስዋለባቸው የአዲስ አበባ ከተማ፣ የሲዳማ እና ሐረሪ ክልሎች ናቸው።

ችግሩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው 54 የምርጫ ክልሎች ውስጥ ግማሽ የሚሆኑት በደቡብ እና ሶማሌ ክልሎች የሚገኙ መሆኑን የምርጫ ቦርድ መግለጫ አሳይቷል። ከሁለቱ በመቀጠል በርከት ያሉ የምርጫ ክልሎቹ በችግሩ ተጽዕኖ የደረሱበት የአማራ ክልል ነው። አፋር፣ ጋምቤላ እና ኦሮሚያ በተከታይነት ሲቀመጡ የድሬዳዋ ከተማ ደግሞ በአንድ የምርጫ ክልሉ ላይ የድምጽ መስጫ ወረቀት ህትመት ችግር ተገኝቶበታል።

የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ‹‹የተፈጠረው ስህተት መስሪያ ቤቱ ኃላፊነት የሚወስድበት ስህተት ነው። እኔም የተቋሙ መሪ ኃላፊነት እወስዳለሁ›› ሲሉ በመስሪያ ቤታቸው ለተፈጠረው ችግር ይፋዊ ይቅርታ ጠይቀዋል። የችግሩ መንስኤ ‹‹ማሻሻያዎችን በትክክል ተረድተው መፈጸም የሚችሉ ባለሙያዎች እጥረት›› ነው ሲሉም ለተሰብሳቢዎቹ ገልጸዋል።

ቦርዱ የተፈጠረውን ችግር ለመቅረፍም ሁለት አማራጮችን እንዳቀረበ ብርቱካን ተናግረዋል። አንደኛው አማራጭ የድምጽ መስጫ ወረቀቶችን በሀገር ውስጥ ማሳተም ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የኅትመት ችግር በተከሰተባቸው የምርጫ ክልሎች ሊካሄድ የነበረውን ምርጫ ከሌሎች አካባቢዎች ጋር ደምሮ ማካሄድ ነው።

በስብሰባው ላይ ከተካፈሉ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ውስጥ በአብዛኞቹ የተደገፈው አማራጭ፤ በድጋሚ የሚታተሙ የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ህትመት በሀገር ውስጥ ማካሄድ ነው። የድጋሚ ህትመቱ ምስጢራዊነቱን ጠብቆ በመንግስታዊው ብርሃን እና ሰላም ማተሚያ ቤት እንዲከናወን ገዢው ፓርቲን ጨምሮ በሶስት ፓርቲዎች ምክረ ሀሳብ ቀርቧል።

የሁለት የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ደግሞ የድጋሚ ህትመቱ በውጭ ሀገር ተከናውኖ ምርጫው ለተወሰኑ ቀናት እንዲራዘም ጠይቀዋል።
የነጻነት እና እኩልነት ፓርቲን በመወከል በስብሰባው ላይ የተገኙ ተሳታፊ በበኩላቸው በሶማሌ ክልል ሊካሄድ የታቀደው ምርጫ ሙሉ በሙሉ በሌላ ጊዜ እንዲካሄድ አሳስበዋል። የሶማሌ ክልል ምርጫ፤ በተለየ የጊዜ ሰሌዳ ምርጫውን ከሚያከናውኑ የምርጫ ክልሎች ጋር በአንድ ላይ እንዲካሄድ ያላቸውን አቋም አንጸባርቀዋል።

ከፓርቲ ተወካዮች የተነሱትን ሃሳቦች እና ጥያቄዎች ያደመጡት የቦርዱ ሰብሳቢ፤ ፈርጠም ያለ ምላሽ ሰጥተዋል። ‹‹ሰኔ 14 ምርጫ እናደርጋለን። ምንም ጥርጥር የለውም›› ሲሉ ምርጫው በድጋሚ እንደማይራዘም አስታውቀዋል።

ፎቶ፡ ኢትዮጵያ ኢንሳይደር

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img