Sunday, November 24, 2024
spot_img

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በክልሉ የተደራጁ ወንጀሎች ተበራክተዋል አለ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ግንቦት 30፣ 2013 ― የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በዋና ከተማው መቀሌና በሌሎች አካባቢዎች፣ በመሣሪያ የታገዙ የተደራጁ ወንጀሎች መበራከታቸውን አስታወቀ፡፡

በትግራይ ክልል ለስድስት ወራት ያህል የቆየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተጠናቆ የፀጥታው ሁኔታ እየተሻሻለ ቢሆንም፣ በመቀሌና በሌሎች ከተሞች በመሣሪያ በመታገዝ በተደራጁ ሰዎች ዝርፊያና ቅሚያ የመሳሰሉ ወንጀሎች መብዛታቸውን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ሙሉቀን ሀፍቴ ተናግረዋል፡፡ በወንጀሎቹ እየተሳተፉ ያሉት ሕወሓት ከእስር ቤት የለቀቃቸው እንደሆኑም ገልጸዋል፡፡

ምንም እንኳ በርካቶቹ ተጠርጣሪዎች ከእስር ቤት የተለቀቁ ቢሆኑም፣ የኅብረተሰቡን ሰላም የማይፈልጉና ሕወሓት ተመልሶ ይመጣል በማለት ለማስፈራራት የተሰማሩ ወጣቶች መኖራቸውንም አክለው ገልጸዋል፡፡ ከእስር ቤት የተለቀቁ እስረኞቸን መልሶ ለመያዝና ወደ ማረሚያ ቤት ለማስገባት የታራሚዎቹን መረጃዎች ሕወሓት ቀድሞ ስላቃጠላቸው፣ አብዛኞቹ የማረሚያ ቤት አስተዳደሮች እንደገና ባለመደራጀታቸው አስቸጋሪ ሁኔታ መፈጠሩን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስረድተዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በትግራይ ክልል ከሁለት ሚሊዮን በላይ ተፈናቃዮች ይኖራሉ ተብሎ እንደሚገመት የገለጹት ዶ/ር ሙሉቀን፣ በርካቶቹ ከጎረቤት አማራ ክልል አዋሳኝ ቦታዎች የተፈናቀሉ ስለሆኑ፣ እነዚህን ዜጎች ወደ ቀዬአቸው መመለስ ቢቻል የሰላሙን ሁኔታ በአመዛኙ መመለስ እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡

በክልሉ የሚገኙ በርካታ የትምህርት ተቋማት ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው ለመጡ ዜጎች እንደ መጠለያ እያገለገሉ እንደሆነ የተለገጸ ሲሆን፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ከዚህ ሳምንት ጀምሮ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው ተመልሰው እንዲማሩ ለማድረግ እየሠራሁ ነው ብሏል፡፡

ምንም እንኳ በጥቂት ትምህርት ቤቶች ትምህርት ሲሰጥ የነበረ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ሕዝቡ ልጆቹን ወደ ትምህርት ቤት እንዲልክና ወደ ግብርና ሥራው እንዲመለስ ከሕዝቡ ተወካዮች ጋር ውይይቶች መቀጠላቸውን ዶ/ር ሙሉቀን ገልጸዋል፡፡

ሕዝቡ ፍርኃትና ጭንቀት ውስጥ እንዲገባ የሚሠሩ አካላት እንዳሉ በመጥቀስም በተለይ በሕዝቡ ውስጥ መረጋጋት እንዳይፈጠር የሚንቀሳቀሱ አካላትን ጊዜያዊ አስተዳደሩ እያደራጀ ባለው በክልሉ ፖሊስ፣ በፌዴራል ፖሊስና በአገር መከላከያ ሠራዊት አማካይነት የሚፈለገውን ሰላም ለማስፈን እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በሌላ በኩል ለሕዝቡ እንዲከፋፈል የቀረበውን ስንዴ በመመሳጠር የሚዘርፉ ‹‹ስግብግብ›› ነጋዴዎችና ግለሰቦች መኖራቸውን በመጥቀስ፣ መሰል የተደራጁ ወንጀሎችን ለማስቆምና ተጠርጣሪዎችን ለሕግ አሳልፎ በመስጠት ረገድ ሕዝቡም የራሱን ሚና ሊወጣ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ ፍራቻ ያደረባቸውን ወላጆች አስመልክተው ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ በደርግ ዘመን አንዱን ከሌላው ለይቶ መደብደብ በማይቻልበት የአውሮፕላን ጥቃት የትግራይ ሕዝብ ልጆቹን ትምህርት ቤት ልኮ ድንጋይ ላይ ያስተምር እንደነበር በማስታወስ፣ አሁን ግን የተመቻቸ ሁኔታ በመኖሩ ልጆቹን መላክና ማስተማር ይገባዋል ሲሉ አሳስበዋል ሲል የዘገበው ሪፖርተር ጋዜጣ ነው፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img