አምባ ዲጂታል፣ እሑድ ግንቦት 29፣ 2013 ― በኢትዮጵያ በተካሄደው የመጀመሪያው የኮሙኒኬሽን አገልግሎት ፈቃድ ጨረታ የተሰረዘበት የደቡብ አፍሪካው ኤምቲኤን ኩባንያ፣ እንደገና በሚወጣው ጨረታ እንደሚሳተፍ አስታውቋል።
ኩባንያው ባለፈው ሳምንት እንደገለጸው፣ ኢትዮጵያ ትልቅ የቴሌኮም ገበያ በመሆኗ ዳግም በሚወጣው የቴሌኮም ፈቃድ ጨረታ ይሳተፋል።
የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ባልቻ ሬባ (ኢንጂነር)፣ የታጠፈውን የቴሌኮም ፈቃድ ጨረታ ዳግም ለማውጣት ባለሥልጣኑ በዝግጅት ላይ መሆኑን ዓርብ ግንቦት 27፣ 2013 ተናግረዋል።
የደቡብ አፍሪካው ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ራልፍ ሙፒታ ወደ ኢትዮጵያ የቴሌኮም ገበያ መግባት የኤምቲኤን የቆየ ፍላጎትና ግብ መሆኑን ገልጸው፣ በተለይ እንደገና በሚወጣው ጨረታ የኢትዮጵያ መንግሥት የሞባይል ባንኪንግ ሥራን የሚፈቅድ ከሆነ ለኩባንያው ትልቅ ዕድል እንደሚሆን አስታውቀዋል፡፡
እንደገና በሚወጣው ጨረታ የፖሊሲ ለውጥ የሚታይ ከሆነ፣ ኩባንያውም በጥብቅ ዲሲፒሊን በመመራት አዲስ በሚሰጠው ዋጋ ላይ እንደሚወስን ገልጸዋል።
የኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ባልቻ (ኢንጂነር) በበኩላቸው፣ እንደገና በሚወጣው ጨረታ አዳዲስ የፖሊሲ አቅጣጫዎች ሊቀመጡ እንደሚችሉና ከእነዚህም መካከል በቴሌኮም መሠረተ ልማት ዝርጋታ መሳተፍ ሊፈቀድ እንደሚችል ጠቁመዋል።
ባለሥልጣኑ በመጀመሪያ ባወጣው ሁለት የቴሌኮም አገልግሎት ፈቃድ ጨረታ ኤምቲኤንና ግሎባል ፓርትነርሺፕ ፎር ኢትዮጵያ የተባለ ጥምረት የተወዳደሩ ሲሆን፣ ከሦስት ሳምንት በፊት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል።
በምክር ቤቱ ውሳኔ መሠረትም ግሎባል ፓርትነርሺፕ ፎር ኢትዮጵያ የተባለው የኩባንያዎች ጥምረት 850 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ በማቅረቡ፣ ይህም ክፍያ ከኤምቲኤን በ29 በመቶ የሚበልጥ በመሆኑ ፈቃዱ እንዲሰጠው ወስኗል።
ኤምቲኤን ያቀረበው ክፍያ አነስተኛ በመሆኑ ጨረታው እንዲሰረዝና በድጋሚ እንዲወጣ መወሰኑም ይታወሳል።
ግሎባል ፓርትነርሺፕ የተባለው ጥምረት በውስጡ የእንግሊዙን ቮዳፎን፣ የደቡብ አፍሪካውን ቮዳ ኮም፣ የኬንያውን ሳፋሪ ኮም፣ የጃፓኑን ሱሚቱሞና የእንግሊዝ መንግሥትን የፋይናንስ ተቋም ሲዲሲና የአሜሪካ አቻውን የያዘ ሲሆን በተጠናቀቀው ሳምንት መገባደጃም ለመክፈል የተስማማውን 850 ሚሊዮን ዶላር ለመንግሥት እንዳስገባ ባልቻ (ኢንጂነር) ይፋ አድርገዋል።
ይህ ኩባንያ ለ15 ዓመት የሚያገለግል ፈቃድ የሚያገኝ ሲሆን በቆይታውም የ8.5 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት በቴሌኮም ዘርፍ ላይ እንደሚያውል፣ የኮሙዩኒኬሽን ሳተላይት በማምጠቅም የ5G እና የ4G አገልግሎትን እንደሚያስፋፋ መግለጹ አይዘነጋም።