Sunday, November 24, 2024
spot_img

ከክልሉ ውጪ ያሉ ሐረሪዎች የብሔራዊ ጉባዔ አባላትን እንዲመርጡ የፀናው ውሳኔ እንዲፈጸም ተጠየቀ

አምባ ዲጂታል፣ እሑድ ግንቦት 29፣ 2013 ― የጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ከክልሉ ውጪ ያሉ ሐረሪዎች የብሔራዊ ጉባዔ አባላትን መምረጥ ይችላሉ በማለት ያፀናውን ውሳኔ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንዲያስፈጽም የሐረሪ ክልል ጠየቀ፡፡

የሐረሪ ክልል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግና በሐረሪ ጉባዔ የተቋቋመው የኢፌዴሪ የሕግ ክርክር ጉዳይ ሰብሳቢ አቶ አዩብ አህመድ እንዳስታወቁት፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትም ሆነ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰጡት ውሳኔ የሐረሪ ጉባዔ ዕጩዎች በክልሉ በሚኖሩ የሐረሪ ተወላጆችና ከሐረሪ ክልል ውጪ በሚኖሩ የሐረሪ ተወላጆች መመረጥ ይችላሉ፡፡ ከሐረሪ ክልል ውጪ ያሉ መራጮች በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥትና በክልሉ ሕገ መንግሥት መሠረት መብታቸው መሆኑን፣ ሰበር ሰሚ ችሎቱ ማረጋገጡን አቶ አዩብ አስታውሰዋል፡፡

ለሰበር ውሳኔ የሕግ ድንጋጌ መሠረት ከሆኑት አንዱ የክልል ምክር ቤቶች አባላት የሚመረጡት በክልሉ ተወላጆች እንደሆነ ገልጸው፣ የክልል ምክር ቤቱን አወቃቀር፣ የምክር ቤት አባላት ብዛትና የክልሉን ልዩ ባህሪ በክልሎች ሕገ መንግሥት መደንገግ ማለት የምርጫ ሕግ ማውጣት እንዳልሆነ ያስረዱት አቶ አዩብ፣ በተመሳሳይ የክልሎች ሕገ መንግሥታት የክልል ምክር ቤቶቻችን አወቃቀርና የክልል ምክር ቤቶች አባላትን ምርጫ በተመለከተ መደንገጋቸውን፣ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥትም ክልሎች ራሳቸውን ለማስተዳደር የተሰጣቸውን መብት የሚያረጋግጥ ዋስትና መሆኑ ተቀምጧል ብለዋል፡፡

በሐረሪ ክልል ሕገ መንግሥት አንቀጽ 50 ንዑስ ቁጥር 2 የሐረሪ ጉባዔ ዕጩዎች በሐረሪ ክልል ውስጥ ነዋሪ በሆኑ ሐረሪዎችና ከሐረሪ ክልል ውጪ ነዋሪ በሆኑ ሐረሪዎች የሚመረጡ መሆኑን ማስታወቁ፣ የክልሉ ምክር ቤት በሁለት ጉባዔ የተዋቀረ መሆኑን መግለጽ፣ በተመሳሳይ የሐረሪ ምክር ቤት አባላት ብዛት 36 መሆኑን፣ የምርጫ ሕግ ማውጣት ብቻ ሳይሆን ክልሉ ራሱን በራሱ የማስተዳደር ዋስትና መስጠት እንደሆነ ያስረዱት ሰብሳቢው፣ ማናቸውም የፌዴራል የመንግሥት አካላትም ሆኑ የክልል መንግሥታት እነዚህን የሕግ ድንጋጌዎች ማክበር እንዳለባቸው፣ ይህ የሕገ መንግሥታቱ ድንጋጌዎች ደግሞ ከኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ድንጋጌ ጋር የማይጋጩ እንደሆነ በተሰጠው ውሳኔ ተረጋግጧል ብለዋል፡፡

‹‹የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኢትዮጵያን ብሔርና ብሔረሰቦች የሥልጣን ባለቤትነታቸውን የሚያረጋግጡበት መሣሪያ የሆነውን ኹነት የሚያስፈጽም ተቋም እንደ መሆኑ መጠን፣ ዜጎች በተቋሙ ላይ እምነትና ተስፋ ሊያሳድሩ ይገባል ብዬ አስባለሁ፤›› ያሉት አቶ አዩብ፣ በዚህ መሠረት ቦርዱ ፍትሐዊና ገለልተኛ ሆኖ ይሠራል ብለው እንደሚያምኑ አስታውቀዋል፡፡

‹‹ቦርዱ ሁሉንም የክልል ሕገ መንግሥታትንም ሆነ የፌዴራሉን ሕገ መንግሥት መሠረት በማድረግ፣ እንዲሁም የፍትሕ ሥርዓቱን በማክበር በፍርድ ቤት የተወሰኑ ውሳኔዎችን በሕግ ማስወሰን ለህልውናው ወሳኝ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ በዚህም የፍርድ ቤት ውሳኔን የማስፈጸም የሕግ ግዴታ ይኖርበታል፤›› ሲሉ አቶ አዩብ ተናግረዋል፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ እንደሰጠ፣ የሐረሪ ጉባዔ በተወሰነው መሠረት እንዲፈጸምለት ፍርድ ቤቱን በፍርድ አፈጻጸም ጠይቋል ያሉት የክልሉ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ፣ አፈጻጸሙ ወደ ሰበር ክርክር ሲሄድ በፍርድ ክርክር እስኪቋጭ ድረስ በሰበር የታገደበት ሁኔታ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ የሰበር ውሳኔውም ከተላለፈ በኋላ ዕግዱ እንደተነሳና በተመሳሳይ በዕለቱ ጉባዔው አቤቱታ በማስገባት አፈጻጸሙ እንዲቀጥል እንደጠየቀ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትም ለሰኞ ግንቦት 30፣ 2013 ቦርዱ ውሳኔውን የማይፈጽምበት ምክንያት ካለ እንዲገልጽ ማዘዙን አቶ አዩብ እንዳረጋገጡለት የዘገበው ሪፖርተር ነው።

አቶ አዩብ አክለውም ቦርዱ ከላይ የተጠቀሱትን መሠረታዊ የሕግ ማስረጃዎችን መሠረት በማድረግ በሐረሪ ክልል ውስጥ ነዋሪ የሆኑ ሐረሪዎችንና ከሐረሪ ክልል ውጪ ነዋሪ የሆኑ ሐረሪዎችን፣ በመጪው ምርጫ የሐረሪ ጉባዔ ዕጩዎችን እንዲመርጡ ምዝገባ በአጭር ጊዜ ይጀምራል ብለው እንደሚያምኑ አስረድተዋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img