አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ግንቦት 28፣ 2013 ― በትግራይ ክልል መቀመጫ በመቐለ ተማሪዎች ከ13 ወራት አስገዳጅ እረፍት በኋላ ከመጪው ግንቦት ሰኞ 30፣ 2013 ጀምሮ መደበኛ የመማር ማስተማር ሂደት እንደሚጀምሩ ተገለፀ።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ በመቐለ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲቋረጥ ምክንያት የነበሩት ችግሮች መፍታታቸውን በመግለጽ፣ በሰባቱ ክፍለ ከተሞች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ከመጪው ሰኞ ጀምሮ ተማሪዎቻቸውን በመቀበል የትምህርት ሂደቱን እንደሚጀምሩ አስታውቋል።
ቢሮው ባለፈው ዓመት በሀገሪቱ ባጋጠመ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ እንዲሁም ዘንድሮ በክልሉ በተፈጠረው የፀጥታ አለመረጋጋት ምክንያት ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ርቀው እንደነበር አስታውሷል።
ለዚህም ዛሬና ነገ በከተማው የሐወዝብ ንቅናቄ ተግባራት ይካሄዳል የተባለ ሲሆን፣ በዚህ እንቅስቃሴ የሚመለከታቸው አጋር አካላት በትብብር እንዲሰሩ ጥሪ አቅርቧል ሲል የዘገበው የትግራይ መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ ነው፡፡