Sunday, September 22, 2024
spot_img

ጄኔራል ሰአረ መኮንንን በመግደል ወንጀል የተከሰሰው አስር አለቃ መሳፍንት ጥጋቡ ጥፋተኛ ተባለ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ግንቦት 27፣ 2013 ― የቀድሞ ጠቅላይ ኢታማዡር ጄኔራል ሰአረ መኮንን እና ሜጀር ጄኔራል ገዛኢ አበራን በመግደል ወንጀል የተከሰሰው አስር አለቃ መሳፍንት ጥጋቡ ጥፋተኛ ተብሏል፡፡

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የፀረ ሽብርና የህገ መንግስት ጉዳዮች ወንጀል ችሎት መዝገቡን መርምሮ ፍርድ ለመስጠት ዛሬ በያዘው ቀጠሮ በችሎት ተሰይሞ ነው በሙሉ ድምጽ የጥፋተኝነት ፍርድ የሰጠው፡፡

ተከሳሹ በሰኔ 15፣ 2011 ጄኔራል ሳአረ መኮንን በዕለቱ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ከነበሩት ከአቶ ታከለ ኡማ ጋር ችግኝ ተክለው ከተመለሱ በኀላ 12 ሰአት ገደማ በባህር ዳር በዶ/ር አምባቸው መኮንን ላይ የተፈፀመውን ግድያ ተከትሎ በአዲስ አበባ መኖሪያ ቤታቸው በስልክ አመራር እየሰጡ ባሉበት ወቅት ወደ ቤታቸው ሊጠይቃቸው ከመጣው ሜ/ጄኔራል ገዛኢ አበራን ጨምሮ በሽጉጥ ተመተው መገደላቸው ይታወሳል፡፡

የአማራ ክልል ሕገ መንግስትን በሀይል ለማፍረስ የፌዴራል መንግስትን ለመቆጣጠር ለታቀደ እቅድ ለማሳካት ተከሳሹ በግንቦት ወር 2011 በጎንደር ከተማ ከጄኔራል አሳምነው ፅጌ በመገናኘት ተልኮ ተቀብሎ በወንጀሉ ተሳትፏል ተብሎ በ1996 የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32/1 ሀ እና ለ፣ 35 /38 እንዲሁም 238 በመተላለፍ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተሳትፎ በህገ መንግስቱና በህገ መንግስታዊ ስርአቱ ላይ በሚፈፀም ወንጀል ተከስሶ ነበር፡፡

ተከሳሹ ወንጀሉን አልፈጸምኩም ሲል የእምነት ክህደት ቃሉን መስጠቱን ተከትሎ ዓቃቤ ህግ የጄኔራል ሰአረ ባለቤትን ኮነሌል ፅጌ እና የጄኔራል ሰአረ አጃቢዎች አጠቃላይ 7 የሰው ምስክርን እና የሰነድ ማስረጃ አቅርቦ አሰምቶ ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱ እንዲከላከል በሰጠው ብይን መሰረት የተከሳሹም ሶስት የመከላከያ ምስክር አቅርቦ የነበረ ቢሆንም በተገቢው ማስተባበል አለመቻሉን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡

በዚህ መልኩ መዝገቡን መመርመሩን የገለጸው ፍርድ ቤቱ የዓቃቤ ህግ ማስረጃ ተከሳሹ ወንጀሉን መፈጸሙ ያረጋገጠ ነው በማለት ጄኔራል ሰአረ መኮንን እና ጓደኛቸውን ሜጀር ጄኔራል ገዛኢ አበራን መግደሉ ተረጋግጧል ሲል ፍርድ ቤቱ በሙሉ ድምጽ ጥፋተኛ ሲል ፍርድ ሰጥቷል፡፡ በዚህ መልኩ የተከሳሹን የቅጣት ማቅለያ ለመመልከት ፍርድ ቤቱ ለሰኔ 11፣ 2013 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

በችሎቱ ጥፈተኛ የተባለው አስራ አለቃ መሳፍንት ጥጋቡ በግራ ጭንቅላቱ ላይ እና በእግሩ ላይ በደረሰው ጉዳት አንድ ዐይኑ እይታው ተጋርዶ እያነከሰ ነበር የተባ ሲሆን፣ ችሎቱም ስላመመህ ቁጭ ብለህ ተከታተል ስለለው ተቀምጦ ፍርዱን ተከታትሏል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img