Sunday, September 22, 2024
spot_img

የአዲስ አበባ ከተማ ለባለሐብቶች የኢንቨስትመንት መሬት ሊሰጥ ነው

– በላይነህ ክንዴ እና አስመራ ሆልዲንግ በዝርዝሩ ተካተዋል

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ግንቦት 27፣ 2013 ― በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ሥራዎች ለመሰማራት አቶ በላይነህ ክንዴን ጨምሮ የተለያዩ ባለሀብቶች ሰፋፊ መሬት እንደተዘጋጀላቸው ተነግሯል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ለውሳኔ አቅርቦታል የተባለው የ16 ኩባንያዎችና ግለሰቦች የኢንቨስትመንት መሬት ጥያቄ ከስፋትና ከመዋእለ ነዋይ አቅም እንዲሁም መሬቱ ከሚገኝበት አካባቢ ጋር ያጣመረ ነው፡፡

መቀመጫውን በተባበሩት ዐረብ ኤምሬትስ ያደረገውና በአፍሪካ አህጉር በማዕድን፣ የባህር ትራንስፖርት፣ ኮንስትራክሽንና ሆቴል ዘርፍ የተሰማራው ‹አስመራ ሆልዲንግ ግሩፕ› ባለ አምስት ኮከብ ሆቴልና አፓርትመንት በ156 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ካፒታል የሚሰራበት 2 ሺሕ 213 ካሬ ሜትር መሬት በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ተዘጋጅቶለታል።

ለዚህ ኩባንያ የታሰበው ቦታ ላይ 29 መኖርያ ቤቶች እንዳሉና ሥፍራውም የመልሶ ማልማት እንቅስቃሴ ያስፈልገዋል ተብሏል።

ጌትአስ ኢንተርናሽናል ኩባንያ ደግሞ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴልና ሞልን በ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ለመገንባት በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ 7 ሺሕ 16 ካሬ ሜትር ቦታ ጠይቆ ውሳኔ እየተጠባበቀ ነው። የተዘጋጀለት ይህ መሬትም ከይገባኛል ነጻ የሆነ እና በመልሶ ማልማት ክልል ውስጥ መሆኑም ተመላክቷል።

በ561 ሚሊዮን ብር ዘመናዊ ሞል ለመገንባት የጠየቁት ደግሞ ታዋቂው ባለሐብት አቶ በላይነህ ክንዴ ሲሆኑ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ውሳኔን የሚጠብቅ 8 ሺሕ 760 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው መሬት በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ተዘጋጅቶላዋል።

አትሌት አበበች ዓለሙ ባለ አምስት ኮኮብ ሆቴል በ500 ሚሊዮን ብር ለመገንባት በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 15 ውስጥ 1 ሺሕ 191 ካሬ ሜትር መሬት ሲዘጋጅላት፣ አርቲስት አደም መሐመድ በተመሳሳይ ክፍለ ከተማና ወረዳ በግማሽ ቢሊዮን ብር ሞል ለመስራት 5 ሺሕ ካሬ ሜትር መሬት ለመረከብ ተዘጋጅቷል። ጀርመን አመንቴ፣ ሶላ ትሬዲንግ እና ወረታ ኢንተርናሽናል ሆቴልና ዘመናዊ ሞል ለመሰራት በቦሌና አራዳ ክፍለ ከተሞች ቦታ ለመረከብ የአዲስ አበባ ካቢኔን የመጨረሻ ውሳኔ እየጠበቁ ይገኛሉ፡፡

ሌሎች ስምንት ኩባንያዎችም ሆቴልና ንግድ ማእከሎችን ለመገንባት በተለያዩ ክፍለ ከተሞች መሬት የተዘጋጀላቸው ሲሆኑ፣ የእነዚህ ግዙፍ የመሬት ጥያቄዎች መቋጫ እንዲያገኝም የካቢኔ ውሳኔ ብቻ እንደሚጠበቅ የዘገበው ዋዜማ ራድዮ ነው፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img