አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ግንቦት 25፣ 2013 ― የዓለም ጤና ድርጅት የቻይናውን ሲኖቫክ የተባለው የኮቪድ-19 ክትባት ለአስቸኳይ አገልግሎት ጥቅም ላይ እንዲውል ፍቃድ ሰጥቷል፡፡
የዓለም የጤና ድርጅት ክትባቱን ከወሰዱ ሰዎች ውስጥ 51 በመቶው የኮሮናቫይረስ የሚያስከትላቸው የህመም ምልከቶች አልታዩባቸውም ያለ ሲሆን፣ ናሙና ከተወሰደባቸው ሰዎች ውስጥ 100 በመቶ ከባድ ምልክቶችን እና ወደ ሆስፒታ ገብቶ መተኛትን መቀነስ እንዳስቻለም ነው የገለጸው፡፡
የዓለም የጤና ድርጅት ባለሙያዎች አሁንም አንዳንድ ማስረጃዎች እና የመረጃ ክፍተቶች ያለመሟላታቸውን ግን አልሸሸጉም።
ይህ ክትባት ከሲኖፋርም ቀጥሎ አረንጓዴ መብራቱን ከአለም የጤና ድርጅት የሚቀበል ሁለተኛው የቻይና ክትባት ሆኗል። ክትባቱን ፍትሃዊ በሆነ የኮሮናቫይረስ ክትባት ማስገኛ ማዕቀፍ በሆነው የኮቫክስ ፕሮግራም ውስጥ እንዲካተት ይህ የዓለም የጤና ድርጅት ፈቃድ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል መባሉንም ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ በበርካታ ሀገራት ጥቅም ላይ እየዋለ የሚገኘው ሲኖቫክ ከ18 ዓመት በላይ ለሆኑ አዋቂዎች የሚመከር ሲሆን፣ ከሁለት እስከ አራት ሳምንት ባለው ግዜ ውስጥ ሁለተኛው ክትባት ይሰጣል።