Sunday, November 24, 2024
spot_img

ለዓመታት ሥራ ያቆመው የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ከ370 ሚሊዮን ብር በላይ ለሠራተኞች ከፍሏል ተባለ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ግንቦት 23፣ 2013 ― በአፋር ክልል አሳኢታ ወረዳ የሚገኘው ተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ከሁለት ዓመታት በላይ ምንም አይነት ምርት እየሰጠ ባይሆንም፣ ከ7 ሺሕ ለሚበልጡ ጊዜያዊ ሠራተኞቹ በየወሩ ክፍያ እንደሚፈጽም እና ለዚህም 378 ሚሊዮን ብር ወጭ ማድረጉን አዲስ ማለዳ ጋዜጣ ዘግቧል፡፡

ስኳር ፋብሪካው ሙሉ በሙሉ ምርት መስጠት ካቆመ ከሁለት ዓመት በላይ ቢያስቆጥርም በፋብሪካው ሲሠሩ ለነበሩ ጊዜያዊ ሠራተኞች ግን አሁንም በየቀኑ የሚታሰብ ከ40 እስከ 45 ብር ክፍያ እየፈጸመ እንደሚገኝ በፋብሪካው ቋሚ ያልሆኑ ሠራተኞችም ተናግረዋል። ይህ ክፍያ በወር እና በዓመት ሲሰላ 378 ሚሊዮን የሚጠጋ ብር ወጭ መደረጉን ያመላክታል።

ፋብሪካው 2 ሺሕ ያክል የድርጅቱን ቋሚ ሠራተኞች ወደተለያዩ የስኳር ፋብሪካዎች ማዘዋወሩንም ሠራተኞቹ ገልጸዋል። የተንዳሆ ስኳር ፕሮጀክት ውስጥ በቋሚነትም ሆነ በጊዜያዊነት የሚሠሩ ሠራተኞች የአካባቢው ተወላጅ የሆኑ ነዋሪዎች እንዲሁም የሸንኮራ አገዳ ተመርቶ ፋብሪካው ሳይገነባ በፊት በስፍራው በነበረው የጥጥ እርሻ ይሠሩ የነበሩ ጭምር መሆናቸውን ገልጸዋል።

ሀብት ንብረት አፍርተው የሚኖሩ ቋሚ ሠራተኞች ራቅ ባሉ ቦታዎች ወዳሉ የስኳር ፋብሪካዎች መዘዋወራቸው ሌላ ቅሬታ ማስነሳቱንም ሠራተኞቹ ገልጸዋል። የስኳር ፋብሪካው ሲገነባ ለሠራተኞች መኖሪያ ተብለው በተገነቡ የመኖሪያ ቤቶች ውስጥ ዛሬም ድረስ የሚኖሩ የድርጅቱ ሠራተኞች እንዳሉም አስተያታቸውን የሰጡ ሠራተኞች ገልጸዋል።

አሁን በተንዳሆ የስኳር ፋብሪካ የአገዳ እርሻ በነበረበት ስፍራ ላይ ስንዴ እየተዘራበት እንዳለም የአካባቢው ነዋሪዎች የገለጹ ሲሆን፣ ስንዴው የሚዘራው ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ በግለሰቦች እንጂ የእርሻው ባለቤት በሆነው መንግሥት እንዳልሆነም አስተያየት ሰጭዎቹ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ በፋብሪካው ይሠሩ የነበሩ ሠራተኞች ደሞዝ በወቅቱ እየተከፈላቸው እንዳልሆነ እና ችግር ውስጥ እንደወደቁ በሰላማዊ ሰልፍ ጭምር ማሳሰባቸውን በአስተያየት ሰጭዎቹ ተገልጿል። ለስኳር ፋብሪካው አገዳ እርሻ የተገነባው የመስኖ ግድብ ከልክ ሲያልፍ ለአካባቢው ነዋሪዎች የጎርፍ ስጋት እንደሆነም ነዋሪዎቹ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ሥር ለሸንኮራ አገዳ ልማት የሚውል 21 ሺሕ ሔክታር ይዞታ የሚገኝ ሲሆን፣ በዚህ ይዞታ ላይ ለምቶ የነበረ የሸንኮራ አገዳ ተክል በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ በቤት እንስሳት ተበልቷል። የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ በ1998 ሥራው ለህንዱ ‹ኦቨርሲስ ኢንፍራስትራክቸር አላየንስ› በይፋ ተሰጥቶ ግንባታው ቢጀመርም፣ በተለያዩ ምክንያቶች በታሰበው መንገድ መሄድ ሳይችል ቀርቶ ግንባታው መጓተቱ የሚታወስ ነው። በሁለት ምዕራፎች የተከፈለው ይህ ፕሮጀክት የመጀመርያው ምዕራፍ 13 ሺሕ ኩንታል፣ ኹለተኛው ምዕራፍም 13 ሺሕ ኩንታል፣ በድምሩ 26 ሺሕ ኩንታል ስኳር በቀን የማምረት አቅም እንደሚኖረው በወቅቱ ተነግሮ ነበር።

የመጀመሪያው ምዕራፍ ፕሮጀክት በ1998 ተጀምሮ በጥቅምት 2007 ቢጠናቀቅም፣ ፋብሪካው የቴክኒክ ችግር ስላጋጠመው፣ ከዚሁ ጋርም ፕሮጀክቱ ረዥም ጊዜ የወሰደ በመሆኑ በ2007 ባጋጠመው ድርቅ ምክንያት የሸንኮራ አገዳው ለከብቶች መኖ እንዲውል ተደርጓል። በወቅቱ በድጋሚ ልማት በ2010 ወደ ምርት እንደሚገባ ቢገለጽም ፋብሪካው እስካሁን ድረስ ምንም አይነት ምርት የማምረት ሙከራ እንዳላደረገ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img