Sunday, September 22, 2024
spot_img

በናይጄሪያ ታጣቂዎች ተማሪዎችን አግተው ወሰዱ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ግንቦት 23፣ 2013 ― በናይጄሪያ ሰሜናዊ ክፍል ከሚገኝ አንድ እስላማዊ ትምህርት ቤት ታጣቂዎች ተማሪዎችን አግተው መውሰዳቸውን ባለሥልጣናት ተናገሩ።

ታጣቂዎቹ ቴጊና ተብላ በምትጠራው ከተማ ከሚገኘው ትምህርት ቤት ትላንት እሑድ ቁጥራቸው እስካሁን በውል ያልታወቀ ተማሪዎች መውሰዳቸውን ቢቢሲ ከባለስልጣናቱ አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡

በዚሁ እገታ አንድ መምህር 150 ተማሪዎች መወሰዳቸውን ሲናገር ሌሎች ደግሞ ታፍነው የተወሰዱት ተማሪዎች ቁጥር ከ200 በላይ ነው ማለታቸውም ነው የተነገረው፡፡

ከጥቂት ወራት በፊት 300 ሴት ተማሪዎች በታጣቂዎች ታግተው ተወስደው ነበር። በወቅቱ ታግተው ከተወሰዱ ተማሪዎች መካከል እስካሁን ያልተለቀቁ ተማሪዎች አሉ።

ዚስ ደይ የተባለ ድረ ገጽ የዓይን እማኞችን ጠቅሶ እንደዘገበው ታጣዊዎቹ በበርካታ ተሽከርካሪዎች ወደ ከተማዋ ከገቡ በኋላ ተኩስ ከፍተዋል።

ታዳጊዎቹ ታፍነው የተወሰዱበት ትምህርት ቤት እድሜያቸው ከ6 እስከ 18 ያሉ ተማሪዎችን ተቀብሎ የሚያስተምር ነው ተብሏል።

የአካባቢው ባለስልጣናት ታጣቂዎቹ በከፈቱት ተኩስ ሁለት ሰዎች በጥይት ከተመቱ በኋላ የአንዱ ሕይወት ማለፉን አረጋግጠዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት በሰሜናዊ ናይጄሪያ ክፍል ቢያንስ ስድስት ጊዜ ያህል የእገታ ወንጀሎች የተፈጸሙ ሲሆን፣ የትምህርት ተቋማት ላይ ባነጣጠሩ እገታዎች ከ800 በላይ ተማሪዎች እና ሠራተኞች ታግተዋል።

በፈረንጆቹ 2014 ቺቦክ ተብላ ከምትጠራው ከተማ 276 ሴት ተማሪዎች በቦኮ ሃራም ቡድን ታፍነው የመወሰዳቸው ዜና በርካቶችን ያነጋገር ክስተት እንደነበር ዘገባው አስታውሷል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img