አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ግንቦት 21፣ 2013 ― በትግራይ ክልል ከተፈናቃዮች መጠለያ ወታደሮች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ወስደዋል መባሉ እጅግ እንዳሳሰበው የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት (የኤንኤችሲአር) ስጋቱን ገለጸ።
የስደተኞች መርጃ ድርጅቱ ቃል አቀባይ ባባር ባሎች ከጄኔቫ በሰጡት መግለጫ ‹‹ሁሉም ወገኖች በኃይል የተፈናቀሉትን ጨምሮ የሰላማዊ ሰዎችን ደሕንነት እንዲያረጋግጡ ከዚህ ቀደም ያቀረብንውን ጥሪ አሁንም እንደግማለን›› ብለዋል።
የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ወታደሮች ከ500 በላይ ወጣት ወንዶች እና ሴቶችን በሽሬ ከተማ ከሚገኝ የተፈናቃዮች መጠለያ በኃይል ወስደው እንዳሠሩ ሦስት የግብረ ሰናይ ሠራተኞች እና አንድ ዶክተር መናገራቸውን ሬውተርስ የዜና ወኪል ከሦስት ቀናት በፊት መዘገቡ ይታወሳል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት ጉዳዩን ካነሳ በኋላ የተወሰኑት መለቀቃቸውን ባባካር ባሎች ቢናገሩም የተለቀቁትን ሰዎች ቁጥር ግን አልጠቀሱም። የተቀሩት ወጣቶች አሁንም በእስር ላይ ይሁኑ ይለቀቁ ግልጽ እንዳልሆነም አክለዋል። ባሎች ‹‹ለጠፉ ሰዎች ዘመዶች ብቻ ሳይሆን በሽሬ ለሚገኙ ተፈናቃዮች በሙሉ ሁኔታው አሳዛኝ እና አሳሳቢ ነው›› ሲሉ ሁኔታውን ገልጸውታል፡፡