Wednesday, October 9, 2024
spot_img

ብልጽግና ፓርቲ ኢትዮጵያ ጫና የበረታባት በቀይ ባህር የነበራትን ተፅእኖ ፈጣሪነት ለመመለስ ተግታ በመሥራቷ ነው አለ

አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ግንቦት 21፣ 2013 ― ለሁለት ቀናት የተሰበሰበው የገዢው ብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በአገራዊና ጂኦ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ መግለጫ አውጥቷል፡፡ በዚህ መግለጫው ‹‹አንዳንድ አካላት ኢትዮጵያ ስትዳከም በቀይ ባህር ላይ ያላቸው ጥቅም የሚሳካ ይመስላቸዋል›› ያለው ፓርቲው፣ ኢትዮጵያ ይህን በፍጹም እንደማትቀበለው አስታውቋል፡፡

ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር ጥቅም ለማግኘት ስታቅድ ከሁሉም ጎረቤት ሀገራት ጋር በሰጥቶ መቀበል መርህ ተስማምታ እንጅ ከማናቸውም ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ ገብታ እንዳልሆነም በመግለጫው ተካቷል፡፡

የኢትዮጵያን ጥቅም በኃይል ወይም በዲፕሎማሲ ተጽዕኖ የማጣት ምንም አይነት ፍላጎት እንደሌለ ሊታወቅ ይገባል ያለው ፓርቲው፣ ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር ያላትን የጋራ ፍላጎቶች በጋራ ለማሳካት ተግባብታ እንደምትሰራ የቀደመ ዲፕሎማሲ ታሪኳ ያሳያል ሲልም ገልጧል፡፡

ኢትዮጵያ የምትገኝበት ጂኦ ፖለቲካዊ ሁኔታ አንደቀደመው ሁሉ የዓለም አይን ማረፊያ ሆኗል የሚለው መግለጫው፤ ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር ጋር አብራ የተፈጠረችና የኖረች ሀገር ናት ብሏል፡፡ ከጥንት ጀምሮ በቀይ ባህር ሲደረግ በነበረው ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊና የንግድ እንቅስቃሴ ላይ ኢትዮጵያ ጉልህ ሚና ነበራት ያለም ሲሆን፤ ብትፈልግ እንኳን ከቀይ ባህር ፖለቲካ ማምለጥ እንደማትችል ገልጿል፡፡


በቀይ ባህር ጥቅም ለማግኘት የምትፈልገው የመልክዓምድር ቅርበት ስላላት በመሆኑ ፍላጎቷ ሌሎች አካላት በአካባቢው ካላቸው ፍላጎት እንደሚለይም ገልጿል፡፡

ኢትዮጵያ የዓባይ ምንጭ በመሆኗ የአፍሪካን ቀንድ እና የሰሜን ምስራቅ አፍሪካ ሁኔታ የመወሰን አቅም እንዳላትም በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡ ሀገሪቱ በአፍሪካ ቀንድ ብሎም በአፍሪካ አህጉር ደረጃ ጠንካራ እየሆነች ከመጣች ጥቅማቸው የሚነካ የሚመስላቸው አካላት ስጋት ውስጥ ሊገቡ እንደሚችሉም ነው በፓርቲው መግለጫ የተካተተው፡፡ ይሁንና ኢትዮጵያ የሌሎች ሀገራት ጥቅም ላይ ስጋት የመፍጠር አላማ እንደሌላትም ፓርቲው አስታውቋል፡፡

በኢትዮጵያ ከመጣው የአመራር ለውጡ በኋላ በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር መሰራቱን ያነሳው መግለጫ፤ የኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነት መታደሱና የተፈጠረው ትብብር ቀጣናውን ለሚታዘቡ ኃይሎች ደስ እንደማያሰኛቸውም አንስቷል፡፡

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር የገባችበት ሁኔታ፤ ሀገራቱ ከነበራቸው የቆየ ወዳጅነትና መልካም ጉርብትና አንጻር ሲታይ ፈጽሞ መፈጠር ያልነበረበት እንደነበር ያነሳው ፓርቲው፤ አሁንም ቢሆን በድንበር አካባቢ የተፈጠረውን ችግር በሰላማዊ ሁኔታ ለመፍታት እንደሚሰራ ገልጿል፡፡

‹‹ሱዳኖች ከመስፋፋትና ከጠብ ጫሪነት ወጥተው ለሰላማዊ መንገድ እንደሚቆሙ ተስፋችን ነው›› ሲል ፓርቲው በመግለጫው ጠቅሷል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img