አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ግንቦት 20፣ 2013 ― ፈረንሳይ በሩዋንዳ ከ27 ዓመታት በፊት በተፈጸመው የዘር ፍጅት ለነበራት ሚና በፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን አማካኝነት አገሪቱን ይቅርታ ጠይቃለች፡፡
ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በሩዋንዳ ይፋዊ ጉብኝት እያደረጉ ሲሆን፣ ኪጋሊ ላይ ለዚህ የዘር ፍጅት መታሰቢያ እንዲሆን በተገነባው ዝክረ-ማዕከል ቆመው ኢማኑኤል ማክሮን ባደረጉት ንግግር ፈረንሳይ እልቂቱ እንደሚመጣ ቀድማ ማስገንዘብ ባለመቻሏ እንዲሁም እውነታው እንዲወጣ ምርመራ ማድረግ ሲገባት ለረዥም ጊዜ ዝምታን በመምረጧ ትጸጸታለች ብለዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው ‹‹እዚህ ለናንተ ክብር ዝቅ ብዬ ከጎናችሁ ቆሜያለሁ፤ ኃላፊነታችንን ለመወጣት ምን ያህል እንዝህላል እንደነበርን ለመረዳት በቅቻለሁ›› ብለዋል፡፡
ነገር ግን ፈረንሳይ በዘር ማጥፋቱ ተሳትፎ እጇ እንዳልነበረበት ማክሮን አበክረው አስገንዝበዋል፡፡ የሩዋንዳው አቻቸው ፖል ካጋሜ የማክሮንን ንግግር አወድሰው ይቅርታ መጠየቃቸው ተገቢ እንደሆነ መናገራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በመጋቢት የተሰየመው የእውነት አፈላላጊ ኮሚሽን ፈረንሳይ በወቅቱ የሩዋንዳው የዘር ፍጅትና እልቂቱን ማስቆም እየቻለች ቸልታን መርጣ ነበር፤ ሆኖም ግን በፍጅቱ እጇ የለበትም ሲል ብያኔ ማሳለፉን ዘገባው አስታውሷል፡፡
በፈረንጁ በ1994 በሩዋንዳ በተፈጸመ እጅግ አሰቃቂ የዘር ፍጅት በመቶ ቀናት ብቻ 800 ሺሕ ሩዋንዳዊያን ተገድለዋል፡፡ በዚያ የዘር ፍጅት በዋናነት የተጨፈጨፉት ቱትሲዎች ቢሆኑም ለዘብተኛ ሁቱዎችም ከሞት አላመለጡም፡፡