አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ግንቦት 19፣ 2013 ― የቀድሞ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም የምስክርነት ጥበቃቸው ተነስቶ ዳግም በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በዛሬው እለትም ወይዘሮ ኬሪያ ዛሬ የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አንደኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀርበዋል።
የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ አወል ሱልጣን እንደገለጹት፤ ወይዘሮ ኬሪያ ከተከሳሽነት ወደ ምስክርነት ተቀይረው ነበር።
ተጠርጣሪዋ በጠቋሚዎችና ምስክሮች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 699/2003 በገቡት ሥምምነት መሠረት ዝርዝር የምስክርነት ቃላቸውን በፈቃዳቸው መስጠታቸውን አስታውሰዋል።
በገዛ ፈቃዳቸው በጽሑፍና በሲዲ ምስክርነታቸውን ሰጥተው እንደነበር ያስታወሱት አቶ አወል፣ በፍርድ ቤት ውሳኔ ከእስር እንደተለቀቁና ጎን ለጎንም ለግለሰቧ አስፈላጊውን የምስክርነት ጥበቃ ሲደረግላቸው መቆየቱን ተናግረዋል።
ይሁንና ወይዘሮ ኬሪያ ቆይተው ምስክር የመሆን ፍላጎት እንደሌላቸው እንዲሁም ምስክርነት ሲሰጡ የቆዩት ተገደው እንደነበር በመግለጻቸው ምስክረነታቸው መቋረጡን ገልጸዋል።
በምስክሮችና ጠቋሚዎች አዋጅ ቁጥር 699/2003 አንቀጵ 11 መሰረት የጥበቃ ተጠቃሚው ሥምምነቱንና ግዴታውን የማያከብር ከሆነ የጥበቃ ስምምነት ውሉ ስለሚቋረጥ አቃቤ ሕግም ለወይዘሮ ኬሪያ ምስክር በመሆናቸው ይሰጣቸው የነበረውን ጥበቃ ለማንሳት መገደዱን ነው አቶ አወል የተናገሩት።
“ከዚህም በኋላ ወይዘሮ ኬሪያ ከዚህ ቀደም በተጠረጠሩበት ወንጀል የቅድመ ምርመራ ስራ እንዲጀመር አቃቤ ሕግ ዛሬ ለፍርድ ቤት ጥያቄ አቅርቧል” ብለዋል።
የተጠርጣሪዋ ጠበቆች በጉዳዩ ላይ ለመከራከር አልተዘጋጀንም በማለታቸው ፍርድ ቤቱ ወይዘሮ ኬሪያ በመጪው ሰኞ ዳግም ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ አዟል።
ወይዘሮ ኬሪያ እስከ መጪው ሰኞ በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንዲቆዩም ፍርድ ቤቱ ወስኗል።