Wednesday, October 9, 2024
spot_img

ኢዜማ በገዢው ፓርቲ ላይ ያለኝ እምነት እየተሸረሸረ ነው አለ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ግንቦት 19፣ 2013 ― የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፓርቲ (ኢዜማ) በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫ ገዢውን ፓርቲ በሀገራችን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲመሰረት ትእግስት ብናሳየውም አካሄዳችንን እንደደካማነት ቆጥሮ በሥልጣን ላይ ለመቆየት እና ምርጫውን እንደከዚህ በፊቱ የይስሙላ ቅቡልነትን ማራዘሚያ ለማድረግ የሚፈጽማቸውን እኩይ ተግባራትን እየፈጸመ ነው ብሏል፡፡

ፓርቲው ‹‹ፍፁም ኃላፊነት የጎደለው›› ነው ያለውን ይህን የገዢውን ፓርቲ ተግባር ወደምርጫው ሲገባ ያስቀመጣቸውን ‹‹ሊሟሉ የሚገቡ አነስተኛ መስፈርቶች በመናድ›› በምርጫው ላይ ያለኝን ሀገርን የማሻገር እምነት በመሸርሸር አገሪቱ ‹‹አሁን ካለችበት ውስጣዊ እና ውጫዊ ጫናዎች አንፃር ፈታኝ ሁኔታ በተሳካ የምርጫ ሂደት ለመውጣት ያላትን ተስፋ በየጊዜው እያደበዘዘው›› እንደሚገኝ ገልጧል፡፡

ፓርቲው ጨምሮም በአገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲመሰረት እና መንግሥት የመመስረቻው ብቸኛ መንገድ ‹‹ሕዝብ ፍላጎቱን በነፃነት በሚገልጽበት ምርጫ መሆን እንዳለበት በማመን ሥልጣንን በአቋራጭ ለመያዝ በተለያዩ አካላት ሲደረጉ የነበሩ ሙከራዎችን ስናወግዝ እና ሀገርን ለማስቀጠል በተቻለን ሁሉ ስንከላከል›› ቆይጠናል በማለት፣ በዚህም ‹‹ከብዙ አካላት ‹ለገዢው ፓርቲ› እንደወገንን ተደርጎ ከፍተኛ ወቀሳ ሲደርስብን ቆይቷል›› ብሏል፡፡

ኢዜማ በመግለጫው በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በመራጮች ምዝገባ ወቅት በገዢው ፓርቲ በኩል ታይተዋል ያላቸውን ችግሮች ያነሳ ሲሆን፣ አሁንም ‹‹ትንሽም ቢሆን ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መመስረት የሚያሳስበው ከሆነ›› ከዚህ ወዲያ ‹‹ከሚፈፅማቸው እኩይ ተግባራት እጁን እንዲሰበስብ እና የሚወሰዱ የእርምት እርምጃዎች ካሉ ሙሉ ተባባሪ እንዲሆን›› ሲል ጠይቋል፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ በሀገርና በሕዝብ ላይ ለሚደርሰው ጉዳት ግን ‹‹እንደ ቀደሙ ገዥዎች፣ የብልጽግና ፓርቲም ከታሪክ ተጠያቂነት›› አያመልጥም ሲል አሳስቧል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img