አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ግንቦት 18፣ 2013 ― በትላንትናው እለት በፍርድ ቤት በእነ ስብሐት ነጋ ላይ አልመሰክርም ማለታቸው የተሰማው የሕወሓት ሥራ አስፈጻሚና የቀድሞዋ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም በቁጥጥር ስር ሊውሉ መሆኑን አምባ ዲጂታል ከምንጮቹ ሰምቷል፡፡
ቀድሞ ለመንግሥት እጃቸውን ሰጥተው በእስር ላይ የነበሩት ወይዘሮ ኬሪያ በሕወሓት ሌሎች መሪዎች ላይ ምስክር ለመሆን “ተስማምተው” ከተከሳሽነት መሰናበታቸው የተነገረ ሲሆን፣ በትላንትናው ችሎት ግን በድጋሚ ሐሳባቸውን ቀይረው ምስክር እንደማይሆኑ ተናግረዋል። ይህንኑ ተከትሎ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በስምምነት ትቶት የነበረውን ክስ በወ/ሮ ኬሪያ ላይ በድጋሚ ሊያቀርብ ተዘጋጅቷል ነው የተባለው፡፡
በሌላ በኩል ዋዜማ ራድዮ ይዞት እንደወጣው ዘገባ ከሆነ ደግሞ የፌዴራል መንግሥት መቀሌን መያዙን ተከትሎ በኅዳር ወር ለመንግስት እጃቸውን የሰጡት ወ/ሮ ኬሪያመ የሕወሓትን የጦርነት ዕቅድ እንዲሁም ድርጅቱ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ሲፈፅማቸው ነበሩ ለተባሉ የተደራጁ ጥቃቶች ብሎም ከጦርነቱ ሽንፈት በኋላ ወደ በረሃ የተደረገውን ሽሽት የተመለከቱ ‹‹ቁልፍ መረጃዎችን›› ለመንግስት በፈቃደኝነት ሰጥተዋል።
ወ/ሮ ኬሪያ ለመንግስት በሰጡት ‹‹ጠቃሚ መረጃ››ና አሳይተውታል በተባለ ከፍተኛ የትብብር መንፈስ የሕወሓት መሪ በመሆናቸው ቀርቦባቸው የነበረውን ክስ በማንሳት የኢትዮጵያ መንግስት ሕግ በሚፈቅደው መሰረት በሕወሓት መሪዎች ላይ ምስክር ለመሆን ‹‹ስምምነት›› ላይ ደርሰዋል። ከስምምነቱ በኋላ ወ/ሮ ኬሪያ መንግስት ጥበቃ ሊያደርግላቸው እሳቸው ደግሞ የጠቅላይ አቃቤ ሕግ ምስክር ሆነው ለመቅረብ ተስማምተው ከእስርም ተለቀዋል፡፡
በእስካሁኑ ሂደት በቪዲዮ በተቀረፀ የምርመራ ቃላቸው ሕወሓት በተለያየ ጊዜ በምስጢር ያደረጋቸውን ውይይቶች፣ የተደረሰባቸውን ስምምነቶች እንዲሁም የጦር መሳሪያ ክምችትን፣ የገንዘብ ዝውውርን፣ ስውር የንግድ እንቅስቃሴዎችን የሚመለከቱ መረጃዎችን ለፌደራል ፖሊስ መርማሪዎች በዝርዝር መናገራቸው ተሰምቷል፡፡
የሕወሓት ስራ አስፈፃሚ እና ማእከላዊ ኮሚቴ መቀሌ ከተማን ለቆ ወደ በረሃ ለመሸሽ በወሰነበት ጊዜ አመራሮቹ የት መደበቅ እንዳለባቸዉ የተወሰነውን ዉሳኔ በዝርዝር የገለፁበት መረጃና ምስክርነት ከሌሎች መረጃዎች ጋር ተጣምረው መንግስት ሲወስዳቸው ለነበሩ ወታደራዊ እርምጃዎች እጅግ ጠቃሚ እንደነበሩና ይህ ትብብር መንግስት ከወ/ሮ ኬሪያ ጋር ‹‹ስምምነት›› እንዲደርስ መተማመኛ ሆኖት እንደነበርም ነው የተነገረው፡፡
ወይዘሮ ኬሪያ በትላንትናው እለት ፍርድ ቤት እንዲመሰክሩ ቢቀርቡም፣ ለፍርድ ቤቱ መመስከር ካለብኝ እንኳ የምመሰክረዉ ይህ መንግሥት በትግራይና በኢትዮጵያ እናቶች፣ ሕፃናትና ሕዝብ ላይ የሚያደርገውን ጭፍጨፋ ከሆነ ብቻ ነው ብለዋል፡፡