አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ግንቦት 17፣ 2013 ― በትግራይ ክልል ሽረ ከተማ የኤርትራ እና የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ሰኞ ምሽት ከ500 በላይ ተፈናቃዮችን በመኪና ጭነው መወሰዳቸውን ሬውተርስ ሦስት የረድኤት ሠራተኞች እና አንድ ዶክተር ነግረውኛል ብሏል።
በቁጥጥር ስር የዋሉት በአብዛኛው ወጣት ወንዶችና ሴቶች መሆናቸው የተነገረ ሲሆን፣ በወቅቱ ድብደባ እንደደረሰባቸውና ገንዘብ ጨምሮ የያዙት ስልክ ተወስዶባቸዋል ተብሏል።
በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የሰሜን ምዕራብ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ቴዎድሮስ አረጋይ በጉዳዩ ላይ ዝርዝር መረጃ ባይኖራቸውም፣ በመቶዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ማረጋገጣቸውን ዘገባው አመልክቷል።
ሬውተርስ የኤርትራውን የማስታወቂያ ሚኒስቴር የማነ ገብረመስቀልን ስለ ጉዳዩ ጠይቄ መረጃውን የሕወሃት ፕሮፓጋንዳ ነው ብለውኛል ሲል አስነብቧል።