አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ግንቦት 17፣ 2013 ― የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንና የግብጹ ፕሬዝዳንት ዐብዱልፈታህ አል ሲሲ ትላንት ሰኞ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ዙሪያ መወያየታቸውን ከሁለቱም ወገን የወጣ መግለጫ አመለከተ።
ሁለቱ መሪዎች በውይይታቸው ስለ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አንስተው መወያየታቸውን ከፕሬዝዳንት ባይደን ጽሕፈት ቤት ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
ከዋይት ሐውስ የወጣው መግለጫ እንደሚያመለክተው በባይደን እና አል ሲሲ በስልክ ባደረጉት ውይይት ላይ ‹‹ፕሬዝዳንት ባይደን የዐባይን ውሃ በተመለከተ ግብጽ ያላትን ስጋት እንደሚረዱ ገልጸዋል›› ብሏል።
ጨምሮም ፕሬዝዳንት ባይደን በጉዳዩ ዙሪያ ‹‹የግብጽን፣ የሱዳንንና የኢትዮጵያን ሕጋዊ ፍላጎቶችን የሚያሟላ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ እንዲገኝ የአሜሪካ ፍላጎት መሆኑን እንደገለጹ›› መጥቀሱን ቢቢሲ ዘግቧል።
ሬውተርስ በሁለቱ መሪዎች መካከል ስለተደረገው ውይይት የግብጽ ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት ያወጣውን መግለጫ ጠቅሶ እንደዘገበው፤ ባይደንን አልሲሲ ‹‹የሁሉንም ወገኖች የውሃና የልማት መብቶችን የሚያስከብር ስምምነት ላይ እንዲደረስ የሚያስችል የተጠናከረ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ለማድረግ ተስማምተዋል›› ብሏል።