Wednesday, October 9, 2024
spot_img

የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ሕግ የሚጥሱ ሚዲያዎችን እያባበልኩ አልቀጥልም አለ

አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ግንቦት 17፣ 2013 ― የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ሕጉን ጠብቀው የማይሠሩ የሚዲያ ተቋማትን በማባበል እንደማይቀጥል አስታውቋል፡፡

ባለሥልጣኑ ከዚህ በኋላ ጥፋት በሚፈጽሙ የሚዲያ ተቋማት ላይ በመረጃ የተደገፈ ርምጃ እንደሚወሰድ በመግለጽ፣ ሕጋዊነት ላይ የሚኖር የድርድር ሒደት አይኖርም ሲሉ የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ አቶ መሐመድ ኢድሪስ ናቸው፡፡

አቶ መሐመድ ኢድሪስ ይህን የተናገሩት የባለሥልጣኑን የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ግንቦት 11፣ 2013 ባቀረቡበት ወቅት ነው፡፡

ከዚህ በፊት የነበረው እንቅስቃሴ ልስላሴው የበዛ፣ ጥሰቶችና ግድፈቶች ሲያጋጥሙ ባለሥልጣኑ የሚሰጣቸውን የዕርምት ማስጠንቀቂያዎች ወይም ግብረ መልስ እንደ ግብዓት ከመውሰድ ይልቅ፣ ውድቅ በማድረግ ባለሥልጣኑ መሳለቂያ የመሆን ደረጃ የደረሰቡት ሁኔታ እንደነበረ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ የሚዲያ ተቋማት ይህን ያህል ሲወርዱ ዝም ብሎ ማየት የባለሥልጣኑ ችግር እንደነበር መናገራቸውን የዘገበው ሪፖርተር ነው፡፡

በሌላ በኩል የመንግሥት ተቋማትና አመራሮቻቸው በሮቻቸውን ለሚዲያ ተቋማት ክፍት በማድረግ ለሕዝብ መድረስ ያለበት መረጃ እንዲደርስ፣ ጋዜጠኞች ሊታገዙ እንደሚገባ አቶ መሐመድ አሳስበዋል፡፡ የመረጃ አሰጣጡ ተቋማት የፈለጉትን ጉዳይ ብቻ አዘጋጅተው መግለጫ በመስጠት እንዲዘገብ መፈለግ መሆን እንደሌለበት ጠቁመዋል፡፡

የመንግሥት ተቋማት ሚዲያዎች በሙሉ ሁነት ላይ እንዲዘግቡ የሚያደርግ አካሄድ ስለሌላቸው፣ ከዚህ በተሻለ መንግሥት ለሕዝቡ የገባው ቃል ምን ደረሰ ብለው ቃለ መጠይቅ ለማድረግ ለሚሄዱ ሚዲያዎች የተዘጉ በሮች መከፈት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

የተሳሳተ መረጃን ማቆም የሚቻለው የመንግሥት አካላት ስለፈጸሙትና እየፈጸሙት ስላለው ሥራ፣ ሚዲያ ሲጠይቃቸው መልስ መስጠት ሲችሉ እንደሆነም ጠቁመዋል።

‹‹ይሁን እንጂ ሚዲያው በዘገባው በአገራዊ ጉዳዮች የማይደራደር መሆን አለበት። ሰላም ብሔራዊ ጥቅማችን ነው፤›› ብለዋል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img