Thursday, November 21, 2024
spot_img

የብልጽግና ፓርቲ አመራሩ የአሜሪካን የቪዛ እቀባ አጣጣሉት

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ግንቦት 16፣ 2013 ― የገዢው ብልጽግና ፓርቲ አመራር የሆኑት አቶ ታዬ ደንደኣ የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ላይ የጣለውን የቪዛ እቅባ ተችተው ጽፈዋል፡፡

አመራሩ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ማስታወሻ ‹‹ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ጥብቅና መቆም ከሁሉም ሰው ይጠበቃል›› ሲሉ ጀምረው ‹‹መርጦ ማልቀስ በራሱ ኢሰብዓዊነት ይሆናል›› በማለት የአሜሪካ መንግሥት ‹‹በሲዳማ ጭፍጨፋ፣ በአኟ ጅምላ ግድያ፣ በኦጋዴን የተራዘመ ሰቆቃ፣ ቄሮና ፋኖ በአጋዚ ሲጨፈጨፍ፣ በኢሬቻ ላይ ጭፎጨፋ፣ በ1997/1998 የአዲስ አበባ ጅምላ ግድያና የማዕከላዊ ስቃዮች›› ለምን እርምጃ አልወሰደም ሲሉ አስታውሰዋል፡፡

‹‹በአስመራ፣ በጎንደርና በባህር ዳር ላይ ሕወሀት ሮኬት ሲተኩስ አሜሪካ ምን ብሏል ያሉት አቶ ታዬ፣ ‹‹ሰሞኑን በጋዛ ህፃናትንና ሴቶችን የጨፈጨፉ የእስራኤል ባለስልጣናትስ የጉዞ ቪዛ ተከልክለዋል›› ወይ ሲሉም ጠይቀዋል፡፡

‹‹ሕዝባችን እጣ ፈንታዉ በመዳፉ መሆኑን ይገነዘባል›› በማለትም ‹‹ሉዓላዊነቱንም በምንም እንደማይለውጥ ዓለም ያውቃል›› ያሉ ሲሆን፣ የቪዛ ክልከላውንም ‹‹የጉዞ ወጪን ይቀንሳል›› ሲሉ አጣጥለውታል፡፡

የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት በኃላፊው አንቶኒ ብሊንከን በኩል ባወጣው መግለጫ አገሪቱ በኢትዮጵያና በኤርትራ የአሁን እና የቀድሞ ባለሥልጣናት፣ በወታደራዊና የደኅንነት ሹማምንት፣ በአማራ ክልል አስተዳደርና የፀጥታ መዋቅር መሪዎች እንዲሁም የሕወሓት መሪዎች ላይ የጉዞ ማዕቀብ መጣሏ መነገሩ የሚታወስ ነው፡፡

ይህ በባለሥልጣናት ላይ የተጣለው ማእቀብ ባለስልጣናቱን ብቻ ሳይሆን ቤተሰቦቻቸውንም የሚያካትት መሆኑን መግለጫው ያመለክታል፡፡ በጉዳዩ ላይ ይህ ዘገባ እስከተሰናዳበት ሰአት ድረስ በመንግሥት በኩል በይፋ የተባለ ነገር የለም፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img