Friday, November 22, 2024
spot_img

በትግራይ ክልል የኬሚካል የጦር መሳሪያ ጥቅም ላይ ውሎ በንጹሐን ላይ ጉዳት መድረሱን ቴሌግራፍ ዘገበ – መንግሥት ዘገባውን መሠረተ ቢስ ነው ብሎታል

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ግንቦት 16፣ 2013 ― በትግራይ ክልል የአገር መከላከያ እና የኤርትራ ወታደሮች ተጠቅመውታል የተባለ ተቀጣጣይ መሳሪያ የያዘው ፎስፎረስ ነው ተብሎ የተገመተ ኬሚካል በንጹሐን ላይ ጉዳት ማድረሱን የእንግሊዙ ዘ ቴሌግራፍ ዘግቧል፡፡

ዘ ቴሌግራፍ በዘገባው በዚሁ በዓለም አቀፍ ሕጎች ጥቅም ላይ እንዳይውል የተከለከለ ነው በተባለው ኬሚካል ጉዳት ደርሶባታል ያላትን ቅሳነት ገብረሚካኤል የተባለች የ13 ዓመት ታዳጊ ታሪክ ይዞ ወጥቷል፡፡

የዜና ተቋሙ ጉዳት ደርሶባታል ያላት ታዳጊ ነግራኛለች እንዳለው ታዳጊዋ የነበረችበት ቤት በከባድ የጦር መሳሪያ መመታቱንና የቤቱ ግድግዳ በእሳት ተያይዞ እሷንም አቃጥሏታል፡፡ ይህንኑ ተከትሎ ወደ ሕክምና ብትወሰድም የተለበለበው የላይኛው የሰውነቷ ቆዳ በሙሉ ተልጧል፡፡

የቅሳነት እናት ናቸው የተባሉት ወይዘሮ ገነት አስመላሽ በበኩላቸው የተተኮሰው ነገር መጥፎ ጠረን እንደነበረው የገለጹ ሲሆን፣ የመርዝ ወይም የኬሚካል ዐይነት ጠረን እንዳለውም አክለዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ በዛሬ እለት መግለጫ ያወጣው የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በክልሉ የኬሚካል ጦር መሣሪያ ተግባራዊ ተደርጓል የሚለውን ይህን የቴሌግራፍ ዘገባ ተችቶ ምላሽ ሰጥቷል፡፡

በሕግ ማስከበር ዘመቻው ኢትዮጵያ ይህ አይነቱን የጦር መሳሪያ በፍፁም አልተጠቀመችም ያለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ አገሪቱ የዓለም አቀፍን ህግ የምታከብርና በማንናቸውም እና በየትኛውም ቦታ የኬሚካል ጦር መሳሪያ ተግባራዊ ሲደረግም ድርጊቱን የምትኮንን ነች ብሏል።

የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ላይ የሚፈበርከውን አሳሳች መሠረተ ቢስ አሉባልታ እንዲያቆም የጠየቀው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ይህ ዐይነቱ አሉባልታና ጫና ተጨማሪ ቀውስ ሊያስከትል የሚችል መሆኑን አንስቶ አስጠንቅቋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img