Sunday, September 22, 2024
spot_img

በሕዳሴ ግድቡ የመጀመርያው ዙር ውሃ ሙሌት ላይ ብቻ ትኩረት ያደረገ ድርድር በቅድሚያ እንዲካሄድ የአፍሪካ ኅብረት መጠየቁ ተሰማ

አምባ ዲጂታል፣ እሑድ ግንቦት 15፣ 2013 ― የወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበርና የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት፣ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የሚካሄደው ቀጣይ ድርድር፣ በቅድሚያ በግድቡ የመጀመሪያ ዙር የውኃ ሙሌት ላይ ብቻ በማተኮር ስምምነት ላይ እንዲደረስበት መጠየቃቸው ተሰምቷል።

ይህን የድርድር አማራጭም የአሜሪካ መንግሥትና የአውሮፓ ኅብረት የደገፉት እንደሆነም ሪፖርተርየዲፕሎማቲክ ምንጮችን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

የወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ፌሊክስ ቲሽስኬዲ ከሳምንት በፊት በግብፅ፣ በሱዳንና በኢትዮጵያ ይህንኑ ጉዳይ የተመለከተ ጉብኝት ማድረጋቸውና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ የሦስቱንም አገሮች መሪዎች አግኝተው መምከራቸው ይታወቃል።

ወደ ሦስቱም አገሮች በመጓዝም የተሻለ ይሆናል ያሉትን የራሳቸውን የድርድር አማራጭ ለአገሮቹ መሪዎች ያቀረቡ መሆኑን የህዳሴ ግድቡ መሠረት ሲጣል ጀምሮ ዋነኛ የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙት አቶ ጌዲዮን አስፋው አረጋግጠዋል።

አዲስ የቀረበውን የድርድር አማራጭ ሰነድ ባይመለከቱም፣ የግድቡ የመጀመሪያ ዙር የውኃ ሙሌት ላይ ብቻ ያታኮረ ድርድር እንዲካሄድ የሚል እንደሆነ መስማታቸውን ጌዲዮን ገልጸዋል።

የመጀመሪያ ዙር ሙሌት ማለት ዘንድሮ የሚካሄደውን የውኃ ሙሌት ብቻ የሚመለከት እንዳልሆነም አስረድተዋል።

የመጀመሪያ ዙር የግድቡ የውኃ ሙሌት በምዕራፎች የሚካሄድ እንደሆነና ይህም ባለፈው ዓመት በግድቡ እስከ 565 ሜትር ድረስ የተከናወነውን የ4.9 ቢሊዮን ሜትር ኩብ የውኃ ሙሌትን፣ ዘንድሮ እስከ 595 ሜትር ድረስ የሚከናወነውን የ13.4 ቢሊዮን ሜትር ኩብ የውኃ ሙሌትና በቀጣይ እስከ 625 ሜትር የግድቡ ከፍታ ድረስ የሚካሄደውን እንደሚያካትት ገልጸዋል።

በግድቡ የውኃ ሙሌት ላይ በሦስቱ አገሮች መካከል ስምምነት ካለመፈረሙ በስተቀር ልዩነት አለመኖሩን የተናገሩት ጌዲዮን አስፋው፣ ይህን የተመለከተ የሙሌት ሠንጠረዥ በሦስቱ አገሮች የቴክኒክ ባለሙያዎች ቡድን ተቀርጾ ስምምነት የተደረገበትና ይህንንም አስመልክቶ አገሮቹ ለተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት በጻፏቸው ይፋዊ የደብዳቤ ልውውጦች ላይ አካተው ያቀረቡ መሆኑን ገልጸዋል።

‹‹ነገር ግን ግብፅና ሱዳን በዚህ የድርድር አማራጭ ላይ ምን ዓይነት ነገር ሊመዙ እንደሚችሉ አይታወቅም፤›› ብለዋል።

በዚህ አዲስ አማራጭ ለመቀጠል ሁለቱ የታችኞቹ አገሮች ከተስማሙ ለኢትዮጵያ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረውም ገልጸዋል።

የግብፁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜ ሽኩሪ፣ ዘንድሮ የሚካሄደው ሁለተኛው ምዕራፍ ሙሌት በግብፅ ላይ የሚያደርሰው ተፅዕኖ እንደሌለ ለአገሪቱ ሚዲያ የተናገሩትም፣ የዴሞክራቲክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት ወደ ግብፅ ተጉዘው አዲሱን አማራጭ ካቀረቡ በኋላ መሆኑን ጠቁመዋል።

ነገር ግን ግብፆች አንድ ነገር ሊመዙ እንደሚችሉ የሚጠረጥሩት ጌድዮን አስፋው (ኢንጂነር) ለዓብነትም የአገሪቱ ሚዲያዎች ስለቀረበው አዲስ ድርድር አማራጭ ሲዘግቡ የቀረበው አማራጭ በቅድሚያ ዘንድሮ በሚካሄደው ሁለተኛው ምዕራፍ የውኃ ሙሌት ላይ ብቻ አድርገው እንደሆነ ጠቁመዋል።

የህዳሴ ግድቡ የመጀመሪያ ዙር ሙሌት ማለት እስከ 625 ሜትር ድረስ የሚከናወነውን የውኃ ሙሌት እንደሚያካትት በመጠቆም፣ የግብፅ ሚዲያዎች ግን ይህንን ከወዲሁ እያምታቱ እንደሆነ ገለጸዋል።

በመሆኑም በወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር የቀረበው የድርድር አማራጭ ምንነትን የተመለከተ ጥርት ያለ ግንዛቤ ከድርድሩ አስቀድሞ ሊኖር እንደሚገባ ተናግረዋል።

በተጨማሪም የግድቡ የመጀመሪያ ሙሌት በሚጠናቀቅበት ወቅት ድርቅ ቢከሰት በማለት የክርክር ነጥቦችን ሊያነሱ የሚችሉ ቢሆንም፣ የዘንድሮን የክረምት ወቅት ጨምሮ በሚቀጥሉት ዓመታት ከፍተኛ የዝናብ መጠን በኢትዮጵያና አካባቢው እንደሚገኝ የአሜሪካው የጠፈር ምርምር ናሳ የሳተላይት መረጃ መሠረት አድርጎ መተንበዩን በመጥቀስ፣ ይህም ለኢትዮጵያ በጎ መሆኑን ጠቁመዋል።

በቀረበው አዲስ የድርድር አማራጭ ላይ ግብፅና ሱዳን እያጤኑት እንደሆነ ከመግለጽ ባለፈ እስካሁን የሰጡት ይፋዊ ምላሽ የለም።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img