አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ግንቦት 14፣ 2013 ― የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በቀጣይ ወር በሚካሄደው አገራዊ ምርጫ ድምጽ መስጠት ሂደቱ በተለያዩ ምክንያቶች ሊከናወንባቸው የማይችልባቸው የምርጫ ክልሎች እና የምርጫ ጣቢዎችን ይፋ አድርጓል።
ቦርዱ ይፋ ባደረገው ዝርዝር የድምጽ መስጠት ሂደቱ የመራጮች ምዝገባ ባልተጀመረባቸው ቦታዎች፣ በጸጥታ ችግሮች የመራጮች ምዝገባ ተጀምሮ በተቋረጠባቸው ቦታዎች እና የመራጮች ምዝገባ ላይ ሂደት ላይ አቤቱታ የቀረበባቸው ወይም ቦርዱ የመራጮች ምዝገባ ሂደቱ ላይ ጉልህ የአሰራር ችግር በማየቱ ማጣራት በወሰነባቸው ቦታዎች እንደማይከናወን ገልጿል።
በዚህም መሠረት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 4 ምርጫ ክልል፣ በሶማሌ ክልል 14 ምርጫ ክልል፣ በኦሮሚያ ክልል ቤጊ፣ ሰኞ ገበያ፣ አያና፣ ገሊላ፣ አሊቦ፣ በአማራ ክልል 8 ምርጫ ክልል ማለትም ማጀቴ (ማኮይ)፣ አርጎባ፣ ሸዋሮቢት፣ ኤፌሶን፣ ጭልጋ 1፣ ጭልጋ እእና ድልይብዛ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል 4 ምርጫ ክልል እንዲሁም የመራጮች ምዝገባ ከፍተኛ የተዛባ አሰራር የታየባቸው እንዲሁም በህግ የተያዘ ጉዳይ ነው ባለው ሐረሪ ክልል በጀጎል ልዩ ምርጫ ክልል፣ ጀጎል መደበኛ ምርጫ ክልል፣ ጀጎል ዙሪያ እና ሁንደኔ ምርጫ ክልልን ጠቅሷል።
በተጨማሪም በጋምቤላ ክልል ዲማ ምርጫ ክልል እና አኮቦ ምርጫ ክልል ከፍተኛ የመሰረተ ልማት እና የመጓጓዥ ችግር ከፍተኛ በመሆኑ በልዩ ሁኔታ የክልል እና የፌደራል መንግስትን ከፍተኛ እገዛ ጠይቋል።