Saturday, November 23, 2024
spot_img

ሐማስ እና እስራኤል የተኩስ አቁም ስምምነት አደረጉ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ግንቦት 13፣ 2013 ― የሁለቱ አካላት ተኩስ አቁም ከተተገበረ በኋላ በርካታ ፍልስጥኤማዊያን በጋዛ ጎዳናዎች ላይ ደስታቸውን ለመግለፅ የወጡ ሲሆን፣ አንድ የሐማስ ባለሥልጣን ‹‹አሁንም ጥይታችንን እንዳቀባበልን ነው›› ሲሉ ተደምጠዋል።

ሁለቱም አካላት በፍልሚያው አሸናፊነታቸውን አውጀዋል። የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን የተኩስ አቁሙ ‹‹ለለውጥ ሃቀኛ እድል የሚሰጥ ነው›› ሲሉም ስምምነቱን ገልፀውታል። ለ11 ቀናት የቆየው ይህ ግጭት እስካሁን የ240 ሰዎችን ሕይወት ሲቀጥፍ አብዛኛው ኅልፈት የተመዘገበው በጋዛ ነው።

በግጭቱ 100 ሴቶች እና ሕፃናትን ጨምሮ 232 ሰዎች በጋዛ ሕይወታቸውን አጥተዋል። እስራኤል ከዚህ ውስጥ ቢያንስ 150 ያህሉ ተዋጊዎች ናቸው ብላለች። ሃማስ እስካሁን ድረስ የሞቱ ተዋጊዎቹን ቁጥር ይፋ አላደረገም።

ትላንት ሐሙስ ብቻ እስራኤል 100 የሚጠጉ የአየር ጥቃቶችን በተለይም በሰሜናዊ ጋዛ ያሉ ሃማስ ይጠቀምባቸዋል ባለቻቸው መሰረተ ልማቶች ላይ የፈፀመች ሲሆን፣ ሃማስ በአፀፋው ሮኬት ተኩሷል።

የእስራኤል የፖለቲካ ካቢኔ የተኩስ አቁሙን ሃሳብ በሙሉ ድምፅ ማፅደቁን ገልጿል። አክሎም ‹‹ የፖለቲካ ክፍላችን የዘመቻው ቀጣይነት የሚወሰነው በመሬት ላይ ባለው ሁኔታ ነው ሲል አፅንኦት ሰጥቷል›› ሲልም አክሏል።

የእስራኤሉ የመከላከያ ሚኒስቴር ቢኒ ጋንትስ የጋዛው ጥቃት ‹‹ያልተጠበቁ ትርፎችን አስገኝቶልናል›› ሲሉ በትዊተር ገፃቸው ላይ አስፍረዋል።

አንድ የሐማስ ባስልጣን ለአሶሺየትድ ፕረስ እንደገለፁት እስራኤል የተኩስ አቁም ማድረጓ እንደትልቅ ድል የሚቆጠር እና ይህም ለእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒናሁ ሽንፈት ነው ብለዋል።

ነገር ግን በሃማስ ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምክር ቤት አባል የሆኑት ባሴም ናይም ስለተኩስ አቁሙ ዘላቂነት ጥርጣሬ እንዳላቸው ነግረውኛል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

የምክር ቤት አባሉ ‹‹ለፍልስጥኤማዊያን ፍትሕ ሳይመጣ፣ እስራኤልን ወረራዋን እና በእየሩሳሌም በሕዝባችን ላይ የምትፈፅመውን የጭካኔ ተግባር ሳታቆም የሚደረግ የተኩስ አቁም ጠንካራ መሰረት አይኖረውም›› ብለዋል።

የሃማስ የፖለቲካ ቢሮ አባል ኢዛት አል-ረሺቅ ለእስራኤል ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።

“እርግጥ ነው ውጊያው ዛሬ ቆሟል። ነገር ግን ኔታኒያሁ እና መላው ዓለም እጃችን በተቀባበለው ጠብመንጃችን ላይ መሆኑን እና ትግላችንም ተጠናክሮ እደሚቀጥል ማወቅ አለባቸው›› ሲሉ ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል፡፡

‹‹ለኔታኒያሁ እና ለሰራዊቱ መግለፅ የምንፈልገው ከተመለሳችሁ እኛም እንደምንመለስ እወቁ ›› ሲሉ አክለዋል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img