አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ግንቦት 12፣ 2013 ― በቅርቡ ኢትዮጵያን ጨምሮ በኤርትራ፣ ሱዳን እና ግብጽ ጉብኝት ያደረጉት የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማን ‹‹ከሕወሓት ጋር ተነጋገሩ የሚል›› ሐሳብ አንስተው እንደነበር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በዛሬው እለት በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል፡፡
ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው ከዚህ በተጨማሪ በምርጫ ጉዳይ ላይም ጄፍሪ ፌልትማን ሐሳብ ሰንዝረው እንደነበር ያስታወሱ ሲሆን፣ ከምርጫው ጋር በተገናኘ ‹‹ምርጫ አታካሂዱ አንልም፤ የአሜሪካ መንግሥትም ለዚህ አላከኝም›› ማለታቸውንም አስታውሰዋል።
በሌላ በኩል ከሕዳሴ ግድብ ጋር በተገናኘም ያነሱት አምባሳደር ዲና፣ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በቅርቡ እንደሚጀመር አስታውቀዋል፡፡
ቃል አቀባዩ የግድቡ ግንባታ 80 በመቶ መጠናቀቁን ያነሱ ሲሆን፣ እስካሁን ለግድቡ ግንባታ 15 ቢሊዮን ብር በሀገር ውስጥ እና በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መዋጣቱን አስታውቀዋል።