አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ግንቦት 11፣ 2013 ― የሁለቱ ክልሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በግልገል በለስ ጉዳዩን አስመልክቶ ውይይት አድርገዋል፡፡ ተፈናቃዮች ዳግመኛ ለጥቃት ተጋላጭ እንዳይሆኑ እና ጥበቃ ለማድረግ እንዲያመች በተመረጡ አራት ማዕከላት ተሰባስበው እንዲኖሩ ይደረጋል፣ አስተማማኝ ሰላም ሰፍኖ ወደየቀያቸው እስኪመለሱ ድረስም በሚኖሩበት አካባቢ ምንም አይነት ችግር እንዳይደርስባቸው ቋሚ ጥበቃ ይደረግላቸዋል ነው የተባለው፡፡
አሁንም የጸጥታ ችግር ስጋት በመኖሩ ምክንያት ተፈናቃዮች በተበታተነ መልኩ ወደ አካባቢያቸው ቢመለሱ ለጥቃት እንዳይጋለጡ ስጋት በመፍጠሩ ነው በተመረጡ አራት ማዕከላት ተሰባስበው እንዲኖሩ ይደረጋል የተባለው፡፡ መከላከያ ሠራዊት የተካተተበት የጋራ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደሥራ እንደሚገባም ተገልጿል።
ለዚህም የአማራና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች መጠለያ ከመገንባት ጀምሮ የጤና፣ የመብራት፣ የውኃና እና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን ያሟላሉ፣ ሌሎች አስፈላጊ ተግባራትንም ኀላፊነት ወስደው ያስተባብራሉ ተብሏል።
እነዚህ ተፈናቃዮች እርሻቸውን በሚያከናውኑበት ጊዜ ለጥቃት ተጋላጭ እንዳይሆኑ በጋራ እየተንቀሳቀሱ እንደሚሠሩና በማሽን የታገዘ የግብርና ሥራ እንዲኖርም ባለሀብቶችን በማሳተፍ ድጋፍ ለማድረግ መታቀዱን ነው የተገለጸው።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን እንደገለጹት ተፈናቃዮችን ለመመለስና ለማቋቋም ምን መሠራት እንዳለበት ውይይት ተደርጓል፤ በአካባቢው ሙሉ በሙሉ ባይሆንም አንጻራዊ ሰላም መስፈኑን አንስተዋል። በዚህም ተፈናቃዮችን በልዩ ሁኔታ መመለስ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በመመካከር መግባባት ላይ መደረሱን ገልጸዋል።
ክረምት ከመግባቱ በፊት ቦታ በመለየትና ምቹ ሁኔታ መኖሩን በማረጋገጥ ተፈናቃዮች ወደቀያቸው እንዲመለሱ የጋራ የሰላምና የልማት ግብረኀይሉ ከነገ ጀምሮ ወደ ሥራ ይገባል ብለዋል። ቤት የተቃጠለባቸውን መርዳት በሚቻልበት ሁኔታ ላይም ሁለቱ ክልሎች በጋራ እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
ክረምቱ ሳያልፍ ፈጥነው ወደ እርሻ ሥራ እንዲገቡም ይደረጋል፤ ከባለሀብቶች ጋር በመነጋገር የእርሻ ትራክተር እንዲገባ ክልሎቹ ይሠራሉ ነው ያሉት። አስተማማኝ ሰላም እስከሚረጋገጥ የጸጥታ አካላት ጥበቃ እንደማይለያቸውም ገልጸዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል ሰላምና የሕዝብ ደኅንነት ቢሮ ኀላፊ ዶክተር ሰማ ጥሩነህ አካባቢው ለልማት የሚመች ነው፣ የሀገሪቱን የወደፊት እጣፈንታ የሚወስኑ የልማት ፕሮጀክቶች ያሉበት መሆኑን ገልጸዋል። ይህንን የሚያውቁ አካላት ሕዝብን ከሕዝብ ለመነጣጠል ባደረጉት ሙከራ ሰብዓዊ ቀውስ ደርሷል ብለዋል። የሕዝብን ህልውና ለማስጠበቅ ክልሉ ይሠራል ያሉት ዶክተር ሰማ ተፈናቅለው በቻግኒ የሚገኙ ወገኖችን ለመመለስ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
የጋራ አመራር የሚሰጥበት ጽሕፈት ቤትም ግልገል በለስ ላይ ይቋቋማል ነው ያሉት። በሂደቱ ክልሉ አብሮ እንደሚሳተፍም አስታውቀዋል። ከሰኞ ጀምሮም ወደተግባር እንደሚገባም አስታውቀዋል።