አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ግንቦት 11፣ 2013 ― በአገሪቱ 11ኛ ክልል ሆኖ ለሚቋቋመው የደቡብ ምዕራብ ክልል መተዳደሪያ ረቂቅ ሕገ መንግሥት መዘጋጀቱን የውሳኔ ሕዝብ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ፀጋዬ ማሞ ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም ክልሉ ከተመሰረተ ከአንድ በላይ ማዕከላት ሊኖረው እንደሚችልም የውሳኔ ሕዝብ አስፈፃሚ ኮሚቴ እና የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት የጋራ ምክክር ማድረጋቸውን ነው የተነገረው፡፡ በቀጣይም በዚሁ ሕገ መንግሥት፣ ባንዲራ እና የክልሉ አርማ ላይ ሕዝቡን ለማወያየት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ምክትል ሰብሳቢው ለቪኦኤ ገልጸዋል፡፡
የክልሉ መመስረተ በራሱ የመጨረሻ ግብ ባይሆንም የአከባቢው ህዝቦች አጥተነው የነበረውን የፍትሐዊ ተጠቃሚነት ችግር እንደሚፈታም ምክትል ሰብሳቢው ጠቅሰዋል፡፡
አሁን ከሚገኙበት የደቡብ ክልል ወጥተው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች የተሰኘ ክልል ለመመሥረት ጥያቄ ያቀረቡት አምስት ዞኖች፣ የቤንች፣ የሸካ፣ የካፋ፣ የምዕራብ ኦሞ ዞን፣ የዳውሮ ዞንና የኮንታ ልዩ ወረዳ ናቸው፡፡