አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ግንቦት 10፣ 2013 ― በኢትዮጵያ የወተት እና የወተት ተዋጽኦ ዘርፍ ላይ ጉልህ ሚና ይኖረዋል የተባለ የማቀነባበሪያ ፋብሪካ በ250 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ሊገነባ መሆኑ ተነግሯል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ይገነባል የተባለው ይሄው ፋብሪካ በቀን 250 ሺሕ ሊትር ወተት የማምረት አቅም ይኖረዋል ተብሏል።
ፋብሪካው የሚገነባው ቦሞጅ ስጋ ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማኅበር በተሰኘ ድርጅት እና መቀመጫውን በዩናይትድ ኪንግደም ባደረገው ዩናይትድ ግሪን ግሩፕ በተባለ ኩባንያ በጋራ ሽርክና ነው።
የቦሞጅ ስጋ ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማህበር 93 በመቶ የሚሆነውን የአክሲዮን ድርሻ በባለቤትነት የያዙት በኦሮሚያ ክልል መንግስት ስር የሚተዳደሩ 21 የልማት ድርጅቶች ናቸው።
መቀመጫውን በአዲስ አበባ ከተማ ያደረገው ቦሞጅ የስጋ ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማህበር 165 ሚሊዮን ብር ይዞ በ21 የአክሲዮን ባለቤቶች የተቋቋመው በ2007 ነበር። ከሃያ አንዱ የአክሲዮን ባለቤቶች 93 በመቶ የሚሆነውን የሚይዙት የመንግስት ልማት ድርጅቶች ናቸው።
የቦሞጅ ተጣማሪ የሆነው ዩናይትድ ግሪን ግሩፕ በግብርና እና ምግብ፣ በታዳሽ ሃይል፣ በፍጆታ ዕቃዎች ምርት እና በሪል ስቴት ዘርፎች የተሰማራ እና በግል የኢንቨስትመንት ቡድን ባለቤትነት ስር ያለ ኩባንያ ነው። ከተመሰረተ 60 ዓመታትን የተሻገረው ኩባንያው በአውሮፓ፣ እስያ እና አፍሪካ ባሉ ሀገራት መዋዕለ ንዋዩን ሲያፈስ መቆየቱን የዘገበው ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ነው፡፡
ዩናይትድ ግሪን ግሩፕ ወደ ኢትዮጵያ ገበያ የገባው በተቀናጀ የግብርና፣ የቁም እንስሳት፣ የወተት ማቀነባበር ልማት ፕሮጀክት ላይ ለመሳተፍ እንደሆነ አስታውቋል። ኩባንያው ከቦሞጅ ጋር የመሰረተውን የሽርክና ፕሮጀክት “ኦሮሚያ ግሪን አግሪ ፉድ” በሚል ስያሜ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እንደተመዘገበ ተገልጿል።