አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ግንቦት 10፣ 2013 ― የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከቀናት በፊት ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ለማካሄድ የሚየስችሉ ቅድመ ሁኔታዎች በወቅቱ ሊጠናቀቁ የሚችሉበት ሁኔታ ስለሌለ ምርጫው በሳምንታት ሊራዘም ይችላል ማለቱ ይታወሳል።
ይህንኑ ተከትሎ በምርጫው ተሳታፊ ከሆኑ ፓርቲዎች መካከል የሆነው የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ቢሮ ኃላፊ አቶ ገለታው ዘለቀ ‹‹ምርጫ ቦርድ ምርጫ አራዝማለሁ ሲል ምን ሊሰራ እንደሆነ በዝርዝር ማሳወቅ አለበት፤ አሁን ላይ ምን እንደሚሰራ ግልጽ የሆነ ነገር የለም›› ተናግረዋል።
‹‹ምርጫ ቦርድ ጊዜ እፈልጋለሁ ሲል ለምንድነው የሚፈልገው የሚል አቋም ነው ያለን›› ያሉት አቶ ገለታው፣ ‹‹ለምሳሌ የሎጂስቲክ እጥረት በእነዚህ ስፍራ አጋጥሞኛል ካለ፤ የሚሰራውን ሥራ እና የሚያስፈልገውን ጊዜ ግልጽ ካደረገ እንስማማለን›› ሲሉ ለቢቢሲ ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል ሌላኛው የምርጫው ተሳታፊ ፓርቲ ኢዜማ የሕዝብ ግንኙነት አቶ ናትናኤል ፈለቀ የድምጽ መስጫው ቀን እንዲራዘም የቀረበውን ሐሳብ ‹‹በእኛ አመለካከት ምክንያታዊ ሆኖ ነው ያገኘነው›› ሲሉ ተናግረዋል። አክለውም ‹‹ምርጫውን አጣድፈን ተገቢ የሆነው ዝግጅት ሳይደረግ ተከናውኖ ችግር ውስጥ ከምንገባ ተጨማሪ ጊዜ ተወስዶ እነዚህን ሥራዎች አጠናቆ ምርጫውን ማካሄድ የተሻለ ውጤት አለው›› ብለዋል።
ከዚሁ ጋር በተገናኘ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ በትላንትናው እለት ምንም እንኳ አስተዳደራቸው በመጀመሪያው ዕቅድ መሠረት ለመቀጠል ፍላጎት ቢኖረውም፤ በምርጫ ቦርድ በኩል ምርጫውን ለአጭር ጊዜ ለማዘግየት ያቀረበው ሐሳብ ‹‹ምክንያታዊ በመሆኑ በዚያው ተስማምተናል›› ሲሉ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።፡
ምርጫ ቦርድ ቀድሞ በያዘው እቅድ መሠረት ከትግራይ በስተቀር በተቀረው የአገሪቱ ክፍል ግንቦት 28፣ በአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ደግሞ ሰኔ 5 የድምጽ መስጫ ቀን ይሆናል ተብሎ ነበር።