Sunday, October 6, 2024
spot_img

ዜና እረፍት ኢትዮጵያዊው የታሪክ እና የማኅበረሰብ ጥናት ባለሞያ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ግንቦት 5፣ 2013 ― ኢትዮጵያዊው የታሪክ እና የማኅበረሰብ ጥናት ባለሞያ አቶ ዓብዱሰመድ ኢድሪስ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ አቶ ዓብዱሰመድ በታሪክ፣ ፖለቲካ እና የማኅረሰብ ጥናት (ሶስዮሎጂ) የላቀ ዕውቀት እንደነበራቸው ይነገርላቸዋል፡፡

በ1947 በድሬዳዋ ከተማ በተለምዶ ጫት ተራ ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ የተወለዱት አቶ ዓብዱሰመድ ኢድሪስ፣ መደበኛ ትምህርት የጀመሩት ‹‹መካሪ መላህላ›› በሚባል የሃይማኖት ት/ቤት ነበር፡፡ መደበኛ ትምህርታቸውን በድሬዳዋ ለገሀሬ ት/ቤት የተከታተሉ ሲሆን፣ በተርም እያለፉ በሦስት ዓመታት ውስጥ ሰባተኛ ክፍል ለመድረስ የበቁ ጎበዝ ተማሪ እንደነበሩም የሚያውቋቸው ተናግረዋል።

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እዚያው ድሬዳዋ በመጨረስ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብተው የነበረ ቢሆንም፣ በዩኒቨርሲቲው የአንደኛ ዓመት ትምህርታቸውን ሲጨርሱ ወደ ኦጋዴን እድገት በኅብረት ዘመቻ ዘምተዋል፡፡ ሆኖም ዘመቻውን ሳይጨርሱበተለያዩ የሕይወት ውጣ ውረድ አልፈዋል።

ኋላም ያቋረጡትን ትምህርት በመቀጠል የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በማኅበረሰብ ጥናት ያጠናቀቁ ሲሆን፣ ህንድ አገር ተጉዘው ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ‹‹ቻይልድ ዌልፌር›› በተባለ ዩኒቨርሲቲ በሶሻል ወርክ አጥንተዋል፡፡

ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በሥራ ዓለም በከፋ ክፍለ ሀገር ጀምረው በድሬዳዋ፣ አሰበ ተፈሪ (ጭሮ)፣ ሐረርና ሌሎች አካባቢዎችን አዳርሰዋል፡፡

አቶ ዓብዱሰመድ በቅርብ ዓመታት ለሐረሪ ክልልና ለሐረሪ ብሄራዊ ሊግ (ሐብሊ) ምስረታ ቁልፍ ሚና እንደተጫወቱ ይነገርላቸዋል፡፡ በተለይ የሐረሪ ክልል ‹‹ክልል 13›› ተብሎ ሲመሰረት የፌዴራሉ መንግሥት በክልሉ አስተዳደራዊ ውሳኔ እንዲሰጡ ከመደባቸው ሦስት አመራሮች መካከል እርሳቸው በጸሐፊነት አገልግለዋል፡፡

አቶ ዓብዱሰመድ ኢድሪስ በተለይ ስለ ሐረር ሕዝብ ታሪክ ባላቸው እጅግ የላቀ የታሪክ እውቀት ለተለያዩ ሥመ ጥር የአገሪቱ ደራሲያን ግብአት ያበረከቱ ነበሩ፡፡ ከነዚህ መካከል ደራሲ ተስፋዬ ገብረአብ እና በእውቀቱ ሥዩም ያሰናዷቸው ታሪክ ቀመስ ሥራዎች ላይ ያላቸው አስተዋጽኦ የሚጠቀስ መሆኑን ወዳጆቻቸው ጽፈዋል፡፡

አቶ ዓብዱሰመድ ኢድሪስ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ባጋጠማቸው የጤና እክል ለተሻለ ሕክምና ወደ ቱርክ አቅንተው ሕክምና ሲያደርጉ ቢቆዩም፣ በትላንትናው እለት በ66 ዓመት እድሜያቸው ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው ታውቋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img