Friday, November 22, 2024
spot_img

ምክትል ጠ/ሚ ደመቀ መኮንን ከአምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማን ጋር ተወያዩ

አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ግንቦት 3፣ 2013 ― የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ ልዑክ አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማንን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡

ውይይታቸው በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር፣ በኢትዮ-ሱዳን የድንበር ጉዳይ፣ በትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታዎች እንዲሁም በተያዠው ወር በሚካሄደው አገራዊ ምርጫ ላይ ያተኮረ መሆኑ ተነግሯል፡፡

አቶ ደመቀ በትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔዎች በተለይም በሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦቶች እና መልሶ ማቋቋም ረገድ እየተከናወኑ ስላሉ ተግባራት፣ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ድርድር አካሄድ፣ መጪው ብሔራዊ ምርጫ ነጻ፣ ፍትሃዊና ሰላማዊ ሆኖ እንዲካሄድ ስለተደረጉ ቅድመ ዝግጅቶች፣ የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ጉዳይ በሰላማዊ መንገድ በድርድር እልባት እንዲያገኝ በኢትዮጵያ በኩል ያለውን ፍላጎት በተመለከተ ለልዩ ልዑኩ አስረድተዋል ተብሏል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በፌስቡክ ገጹ እንዳስታወቀው፣ በተያያዘም በኢትዮጵያ እና አሜሪካ መካከል በተለያዩ ዘርፎች ያለውን ትብብር አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ አቶ ደመቀ ገጸዋል።

አምባሳደር ጄፍሪ ፈልትማን በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለአሜሪካ ስትራቴክ አጋር መሆኗን ጠቅሰው፣ በሰላምና መረጋጋት ጉዳዮች በትብብር ለመስራት ያላቸውን ፍላጎት መግለጻቸውንም ሚኒስቴሩ ስታውቋል።

አያይዘውም የሕዳሴ ግድብን የሦስትዮሽ ድርድር በማስቀጠል በሁሉም ተደራዳሪ አካላት ዘንድ ተቀባይነት ያለው መፍትሔ ላይ ለመድረስ በሚደረገው ጥረት በሀገራቸው በኩል አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።

ከሰሞኑ በግብፅ፣ በኤርትራ እና በሱዳን መሰል የስራ ጉብኝት ያደረጉት አምባሳደር ፌልትማን ወደ ኢትዮጵያ የገቡት በትናንትናው ዕለት ሲሆን፣ ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ ወዲህ ከኢትዮጵያ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ስለሺ በቀለ ጋር ተወያይተዋል፡፡

አምባሳደሩ በሱዳን በነበራቸው ቆይታ በሕዳሴው ግድብ ጉዳይ በአፍሪካ ሕብረት መሪነት የተጀመረው ድርድር እንዲቀጥል ማሳሰባቸው ይታወሳል፡፡ ሦስቱም ተደራዳሪ ሀገራት ካልፈቀዱ በስተቀር አሜሪካ ጣልቃ የመግባት ፍላጎት እንደሌላትም ነው የገለጹት፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img