አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ግንቦት 3፣ 2013 ― በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱት ሳልሳይ ወያነ፣ ባይቶና እና ውድብ ናፅነት የተባሉ ፓርቲዎች ባወጡት መግለጫ ሕወሓት አሸባሪ ተብሎ መሰየሙን ተቃውመውታል፡፡
የሕወሃት በሽብርተኝነት መፈረጅ በትግራይ ሕዝብና የትግራይ ተወላጅ ሊሂቃን ላይ ጭፍጨፋ ለማካሄድ ታስቦ የወጣ የሕግ ከለላ ነው ያሉት ፓርቲዎቹ፣ በተደረገው ፍረጃ ‹‹ከፓርቲው ጋር የተግባር ወይም የሐሳብ መመሳሰል ያለው በሚል በመሆኑ›› ጉዳዩ የሕወሃት ብቻ አይደለም ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ ለአሜሪካ ድምጽ የተናገሩት የፓርቲዎቹ ተወካይ ዶክተር ደጀን መዝገበ ፍረጃው ሁሉም ቤት የሚገባ ነው ያሉት ሲሆን፣ ፓርቲዎቹ ውሳኔውን ያሳለፈውን ምክር ቤትም ሕጋዊ አይደለም ብለው እንደሚያምኑ ነው የገለጹት፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ አቃቢ ሕግ በበኩሉ ሕዝብና ፓርቲ የተለያዩ ናቸው ያለ ሲሆን፣ የወጣው ዐዋጅም ሕወሓትና አባላቱን ብቻ የሚመለከት ነው እንጂ ጠቅላላ ሕዝቡን የሚመለከት እንዳልሆነ ግልፅ ነው የሚል ምላሽ ሰጥቷል።
ሦስቱ ፓርቲዎች ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ በትግራይ ክልል ያለውን ጦርነት በተመለከተ ለአፍሪካ ኅብረት ደብዳቤ መጻፋቸው የሚታወስ ነው፡፡