አምባ ዲጂታል፤ ሐሙስ መጋቢት 26፣ 2016 – ሱማሊያ በአገሯ የሚገኙትን የኢትዮጵያ አምባሳደር ሙክታር መሐመድን ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ ማድረጓን የዘገበው ሬውተርስ ዜና ወኪል ነው፡፡ የዜና ወኪሉ አምባሳደሩ ወደ ኢትዮጵያ እንደተሸኙ ከሁለት የሱማሊያ ባለሥልጣናት ሰምቻለሁ ብሏል፡፡
ሱማሊያ አምባሳደር ሙክታር መሐመድን ወደ አዲስ አበባ ከመሸኘቷ በተጨማሪ በፑንትላንድ እና ሱማሊላንድ የሚገኙ የኢትዮጵያ ቆንስላዎችን መዝጋቷንም ዘገባው ጨምሮ አመልክቷል፡፡ ይህ የሱማሊያ ውሳኔ የመጣው በትላንትው እለት በፑንትላንድ የፋይናንስ ሚኒስትር የተመራ ልዑክ ማነጋገራቸውን ካሳወቁ በኋላ ነው፡፡ የፋይናንስ ሚኒስትሯ አዲስ አበባን የጎበኙት ፑንትላንት ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ከሶማሊያ ፌዴራል መንግሥት ጋር የሚኖረኝ ግንኙነት አብቅቷል ማለቷ ይታወሳል፡፡
አሁን በአገሯ የሚገኙትን የኢትዮጵያ አምባሳደር ወደ አዲስ አበባ የሸኘችው ሱማሊያ በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ኢትዮጵያ ከሱማሌላንድ ጋር የወደብ መግባቢያ ስምምነት መፈረሟን ተከትሎ ቅሬታዋን ስትገልጽ መቆየቷ ይታወቃል፡፡ በጉዳዩ ላይ ኢትዮጵያ መንግሥት እስካሁን ምላሽ አልሰጠበትም፡፡