አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ሚያዝያ 30፣ 2013 ― ቦርዱ ውሳኔውን ያሳለፈው በመራጮች ምዝገባ ሂደቱ ላይ የቀረቡትን ዝርዝር አቤቱታዎች በስፋት ከመረመረ በኋላ መሆኑን በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።
ቦርዱ ከፓርቲዎች በተለያ ጊዜ በጋራ እና በተናጠል የቀረቡለት አቤቱታዎች ያተኮሩባቸው አንኳር ጉዳዮች መካከል የመራጮች ምዝገባ ካርዶች የማይገባቸው ሰዎች እጅ መግባታቸውን፣ ያልተሞሉ የመራጮች ምዝገባ ካርዶች ለዝቅተኛው መንግስት እርከን መሰጠታቸውን፣ የመራጮች ምዝገባ ሂደቱን የገዥው ፓርቲ የዝቅተኛ እርከን ሰራተኞች ከፍተኛ ጣልቃገብነት ነው መሠራቱን፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች ከመንግስት አስተዳደር እርከን ሰራተኞች እና እጩዎች ጋር በዝምድና እና በተለያዩ መንገዶች የተያያዙ በመሆናቸው የገለልተኝነት ጥያቄ መኖሩን፣ የተቃዋሚ ፓርቲ ደጋፊዎች ናቸው ተብለው የሚታሰቡ ዜጎች እንዳይመዘገቡ ክልከላ መደረጉን፣ የመራጮች ካርድ የወሰዱ ዜጎች እጅ ተመልሶ መሰብሰቡን እና የመራጮች ካርድ ብሉ ቦክስ በምርጫ ጣቢያዎች ሲደርስ በተገቢው መንገድ ሳይታሸግ ተከናውኗል በሚሉ ላይ መሆኑን ዘርዝሯል።
ምርጫ ቦርድ ውሳኔውን ያሳለፈባቸው አራቢ፣ ደግሃመዶ፣ ጎዴ፣ ጂጂጋ 1፣ ቀብሪደሃር፣ ደበወይን፣ ቀላፎ እና ዋርዴር ናቸው።
ምርጫ ቦርድ በመግለጫ ላይ እንዳመለከተው፤ አቤቱታ በቀረበባቸው የምርጫ ክልሎች ላይ ያለውን የመራጮች የምዝገባ ሂደት የሚያጣራ ቡድን እንደሚያቋቁም ገልጿል።
በዚህ የማጣራት ሂደት ውስጥ የአቤቱታ አቅራቢ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የቦርዱ ሰራተኞች እና ገለልተኛ ባለሙያዎች እንደሚሳተፉም ቦርዱ ጠቁሟል።
እነዚህ አካላት የማጣራት ሂደቱን እንዴት ሊያከናውኑት እንደሚገባ የሚመራ የቴክኒክ ዝርዝር መመሪያ ከተዘጋጀ በኋላ ወደ ተግባር እንደሚገባም ገልጿል።