አንጋፋው ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ቀድሞ በሥፋት ከሚታወቅበት ‹‹የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን (ኢሳት)›› በመውጣት በዚያው ከነበሩ ባልደረቦቹ ጋር ባንድነት ከመሠረተው ‹‹የኢትዮጵያ ሚዲያ ሰርቪስ (ኢኤምኤስ)›› ጋር መለያየቱን አሳውቋል፡፡ ጋዜጠኛ ሲሳይ ይህንኑ በይፋዊ የትዊተር ገጹ ላይ ዛሬ ነሐሴ 17፣ 2015 ማለዳ ላይ አስፍሯል፡፡
ጋዜጠኛው ከኢኤምኤስ ጋር ለመልቀቁ ምክንያቱ ምን እንደሆነ የገለጸው ነገር ባይኖርም፤ ‹‹የእኔ ከኢኤምኤስ መልቀቅ ለእኔም ሆነ ለተቋሙ እንዲሁም ለመላው የኢኤምኤስ ባልደረቦች አስፈላጊ እንደሆነ›› አምኛለሁ ሲል ጽፏል፡፡ ኢኤምኤስን ከመልቀቁ አስቀድሞ በነበሩት ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በሚዲያው እለታዊ ዝግጅት ላይ ተሳትፎ ማድረግ አቁሞ የነበረው ሲሳይ፤ በዚህ ጊዜ የጠፋው ‹ረፍት ላይ› ስለነበረ መሆኑንም ገልጧል፡፡ በዚህ ‹‹የረፍት›› ባለው ጊዜ ‹‹ነገሮችን በመገምገም›› መቆየቱንም አስፍሯል፡፡
ከመሠረተው ኢኤምኤስ ጋር መለያየቱን ይፋ ያደረገው ሲሳይ አጌና ጋዜጠኝነትን በፍሪላንሰርነት የጀመረው በ1987 ነበር፡፡ ብዙም ሳይቆይ ‹‹ዛጎል›› የተሰኘ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ መሆን የቻለ ሲሆን፣ ከ1988 እስከ ኅዳር 1998 ድረስ ደግሞ ከፍተኛ ዝና ባተረፈበት ‹‹ኢትኦጵ›› ጋዜጣ እና መጽሔት ዋና አዘጋጅነት ሠርቷል፡፡ ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና በዋና አዘጋጅነት ይመራው የነበረው ኢትኦጵ ጋዜጣ በምርጫ 97 ወቅት የኅትመት ሥርጭቱ 130 ሺሕ ደርሶ እንደነበር ይነገርለታል፡፡
ምርጫ 97ን ተከትሎ በተከሰተው ፖለቲካዊ ቀውስ ምክንያት ከታሠሩ 15 ጋዜጠኞች መካከል አንደኛው የነበረው ሲሳይ አጌና፤ በዚሁ ሰበብ ለአንድ ዓመት ከመንፈቅ በቃሊቲ ማረሚያ እስር ላይ ቆይቷል፡፡ ከዚሁ እስር ጋር በተገናኘ ‹‹የቃሊቲው መንግሥት›› የሚል ርእስ ያለው መጽሐፍ ለአንባቢያን አድርሷል፡፡
ሲሳይ አጌና ከእስር ቤት መልስ በዋና አዘጋጅነት ይሠራበት የነበረው ኢትኦጵ ጋዜጣን ለመመለስ ሙከራ ቢያደርግም በወቅቱ በነበረው የኢህአዴግ አገዛዝ ክልከላ እንደተደረገበት ይናገራል፡፡ ከዚህ በኋላ ለጥቂት ጊዜያት የኢትዮጵያን ፖለቲካ የተመለከቱ ጉዳዮችን በሚያነሱ ድረ ገጾች ላይ የሠራው ሲሳይ፤ በመጨረሻ ወደ ስደት አቅንቶ ነፍጥ አንግቦ ሲንቀሳቀስ የነበረው ‹‹የግንቦት 7›› ድምጽ ነው ይባል በነበረው ኢሳት ውስጥ ለረዥም ዓመታት በመሥራት ይታወቃል፡፡
ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና በስደት ከቆየበት አሜሪካ ወደ አገር ቤት የመመለስ ዕድል ያገኘው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በ2010 ወደ ሥልጣን መንበር ከወጡ በኋላ ነበር፡፡ በየካቲት 2011 በአዲስ አበባው ሚሊንየም አዳራሽ በተዘጋጀ ፕሮግራም ላይ ‹‹ሲሳይ አጌና የኢትዮጵያ ጀግና›› በሚል በታዳሚው የተዘመረለት ጋዜጠኛው፤ በወቅቱ አዲስ በነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሙገሳ ከተቸሯቸው ጥቂት ጋዜጠኞች መካከል ነበር፡፡
ሲሳይ አጌና ከዚህ በኋላ ወደ ስደት አገሩ አሜሪካ በመመለስ በኢሳት ዝግጅቶችን ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ በዚህ ጊዜ ‹‹የለውጥ›› የሚባለውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሚመሩት ሥርዐት የበዛ ድጋፍ እና ርህራሄ ያሳያል በሚል ነቀፌታ የሚሰነዝሩበት ነበሩ፡፡ በፍጥነት በተቀያረው የኢትዮጵያ ፖለቲካ መድረክ ላይ ይህንኑ አስተያየት በተለይ ኋላ ላይ ከጋዜጠኞቹ ፋሲል የኔዓለም እና መሳይ መኮንን ጋር በመሠረተውና አሁን ከተለየው ኢኤምኤስ ላይ የሚያንጸባርቁ ተመልካቾችን አፍርቶ ነበር፡፡
የጋዜጠኝነት ሕይወቱ ወደ 30 ዓመት እየተጠጋ የሚገኘው ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና አሁን ከኢኤምኤስ ጋር መልቀቁን በገለጸበት ጽሑፍ፤ በቀጣይ በሌላ የሚዲያ አማራጭ ስለመመለሱ አልያም ይህ ውሳኔው ከሚዲያ ጋር እስከመጨረሻው የተለያየበት ስለመሆኑ ያሠፈረው ነገር የለም፡፡ [አምባ ዲጂታል]