Wednesday, December 4, 2024
spot_img

ባንኮች ከወለድ ነፃ ከሰበሰቡት ተቀማጭ ገንዘብ ውስጥ ለብድር የዋለው መጠን ከ30 በመቶ ያለፈ አይደለም ተባለ

አምባ ዲጂታል፤ ሰኞ ግንቦት 21፣ 2015 – በ2015 ሒሳብ ዓመት በዘጠኝ ወራት ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በሚሰጡ ባንኮችና አገልግሎቱን በመስኮት ደረጃ በሚያቀርቡ 14 ንግድ ባንኮች ከ163.7 ቢሊዮን ብር በላይ ከወለድ ነፃ ተቀማጭ ገንዘብ ያሰባሰቡ ቢሆንም፣ ከዚህ ውስጥ ለብድር አገልግሎት የዋለው ከ30 በመቶ እንደማይበልጥ ተገልጿል።

አንዳንድ ባንኮች ከወለድ ነፃ ካሰባሰቡት ተቀማጭ ገንዘብ መልሰው ፋይናንስ በማድረግ ረገድ የተሻለ አፈጻጸም ቢያሳዩም፣ ከፍተኛ መጠን ያለውን ከወለድ ነፃ ተቀማጭ ገንዘብ ያሰባሰቡት እንደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያሉ ባንኮች ግን በሰበሰቡት ልክ ፋይናንስ እያደረጉ አለመሆኑ ታውቋል፡፡ 

በዘንድሮ በጀት ዓመት የአገር ውስጥ ባንኮች በአጠቃላይ ካሰባሰቡት 163.7 ቢሊዮን ብር የወለድ ነፃ ተቀማጭ ገንዘብ ውስጥ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 88.1 ቢሊዮን የሚሆነውን ድርሻ በመያዝ በቀዳሚ ደረጃ ላይ ተቀሞጧል። ከዚህ ውስጥ ግን ለብድር ያዋለው 18.8 ቢሊዮን ብር ወይም 19 በመቶውን ብቻ እንደሆነ ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል።

ባንኮቹ ዘንድሮ ያሳየት ውጤት ቀደም ባሉት ዓመታት የነበረው አፈጻጸም ጋር ተመሳሳይ መሆኑም ነው የተገለፀው።

በ2014 የሒሳብ ዓመት ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ከተሰባሰበው 117.2 ቢሊዮን ብር ውስጥ ፋይናንስ ወይም ለብድር የዋለው 35.5 ቢሊዮን ብር ብቻ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መረጃ ያመለክታል። ከዚህ ውስጥ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 69.6 ቢሊዮን ብር ከወለድ ነፃ ተቀማጭ ገንዘብ ያሰባሰበ ሲሆን፣ ፋይናንስ አድርጎት የነበረው ደግሞ 9.3 ቢሊዮን ብር ብቻ እንደነበር መረጃው ያመለክታል፡፡

በሚሰበሰበው ተቀማጭ ገንዘብ ልክ ፋይናንስ አለመደረጉ ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ እንዳለው የሚታመን ሲሆን፣ ለዚህ ችግር መንስዔ ደግሞ የተለያየ ምክንያቶች መኖራቸውን የዘርፉ ተዋናዮች ያስረዳሉ።

የዘምዘም ባንክ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መሊካ በድሪ፣ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ተቀማጭ ገንዘብ መጠን በጣም እያደገ መሆኑን ጠቀሰው፣ ነገር ግን የሚሰበሰበውን ያህል ፋይናስ እየተደረገ አለመሆኑ ሊያሳስብ እንደሚገባ ይጠቁማሉ፡፡ ‹‹በአሁኑ ወቅት ከወለድ ነፃ ተቀማጭ ገንዘብ መጠኑ በጣም እያደገ ነው›› ያሉት ወ/ሮ መሊካ፣ ነገር ግን የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑ ባደገበት መጠን ልክ ፋይናንስ አለመደረጉ ጤናማ እንዳልሆነ በተለያዩ መድረኮች በተደጋጋሚ ማንሳታቸውን አስረድተዋል፡፡ የችግሩ ምንጭ የተለያዩ ምክንያቶች የሚቀርቡበት ቢሆንም፣ ደንበኛው ራሱ ፍላጎቱንና ሞዴሉን አውቆ ምን ያህል ለመገልገል ተዘጋጅቷል? የሚለው ጉዳይ በቀዳሚነት የሚጠቀስ መሆኑን ወ/ሮ መሊካ ይገልጻሉ፡፡ አገልግሎቱን በሚገባ ከማስተዋወቅ አንፃርም ያለው ክፍተት አንዱ ችግር መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ኑሪ ሁሴን እንደሚገልጹትም፣ ከወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት ፋይናንስ የተደረገው መጠን ከተቀማጭ ገንዘቡ ጋር ያልተጣጣመው በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ እንደሆነ፣ ከእነዚህም ውስጥ እንዱ የብድር አገልግሎቱን ሊያሳድግ የሚያስችል በቂ የሕግ ማዕቀፍ አለመኖር እንደሆነ አመልክተዋል።

በእሳቸው እምነት ሊስተካከሉ የሚገባቸው ጉዳዮች ቢኖሩም አሁን ለብድር የዋለው ገንዘብ መጠንና ዕድገቱ ጥሩ ስለመሆኑ ይገልጻሉ፡፡   
ሌሎች የባንክ የሥራ ኃላፊዎችም እየተሰበሰበ ያለውን ተቀማጭ ገንዘብ መልሶ ለብድር ለማዋል ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት መሥፈርቶችን የሚያሟሉ የተለያዩ አገልግሎቶችን ሥራ ላይ ማዋል እንደሚገባ ይጠቅሳሉ። ስለአገልግሎቱ በቂ ግንዛቤ መስጠትና ወደ ተገልጋዩ መቅረብ የሚያስፈልግ ሲሆን፣ በዚህ ረገድ ብዙ አለመሠራቱ በአንዳንድ ባንኮች ከሚሰበሰበው ተቀማጭ ገንዘብ አብዛኛው ፋይናንስ ሳይደረግ ለመቅረቱ አንዱ ምክንያት ይኼው የግንዛቤ ችግር መሆኑን ይስማሙበታል፡፡

ከባንኮችም አንፃር ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚያስፈልጋቸውን አገልግሎቶች እየሰፋና በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚሠራበት መልኩ ተቀማጭ ገንዘቡ ፋይናንስ የማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ በሽርክና አብሮ የሚሠራባቸው አሠራሮችንም ሥራ ላይ ማዋል ሲጀመር እያደገና እየተሻሻለ የሚመጣ መሆኑን ወ/ሮ መሊካ ተስፋ ያደርጋሉ፡፡

ብሔራዊ ባንክም ለዚህ ምቹ ሁኔታዎችን የሚፈጥር መመርያዎችን ሲያወጣና የፖሊሲ ማሻሻያዎች እየተደረጉ ሲሄዱ፣ በተቀማጭ ገንዘብና በፋይናንሱ (በብድሩ) መካከል ያለው ክፍተት እየጠበበ ይሄዳል ብለው እንደማያምኑ ጠቅሰዋል፡፡ 

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img