‹‹ሁላችሁም ወገኖቻችን ማወቅ ያለባችሁ፣ እዚህ ያለውን የኔን ችግር የማውቀው እኔ ነኝ››
አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ሚያዝያ 30፣ 2013 ― የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን መሪ የሆኑት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በትግራይ ክልል ይካሄዳል ያሉትን ‹‹የአረማዊነት›› ተግባር ከዚህ ቀደም አውግዘው ቢናገሩም በተደጋጋሚ ለሕዝብ እንዳይደርስ መታፈኑን በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች በተሠራጨ የቪድዮ ንግግራቸው ላይ ገልጸዋል፡፡
በውጨ ሀገር ዜግነት ባለው የአቡኑ ወዳጅ በእጅ ስልክ በተቀረጸው የ14 ደቂቃ የቪዲዮ መልእክታቸው በትግራይና በሀገሪቱ የተከሰቱ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ሐሳብ ገልጸዋል።
‹‹ስድስት ወር ሙሉ አፋችን ተለጉሞ፣ በፍርሐት እና በተጽእኖ እስካሁን አልተናገርንም›› ያሉት አቡነ ማትያስ፣ ሚያዝያ 7 ያደረግኩት ኢንተርቪው ታግዷል፤ ስቃወም ድምጼ ይታፈናል፤ የዓለም ሚዲያ እየተናገረው እኛ እንዳንናገር ታፍነናል፣ እናገራለሁ ይመልሱታል፤ ይኸው እስከአሁን ጊዜ ምንም አይነት ፍቃድ አልተገኘም» ሲሉ በሥም በውል ያልጠቀሱትን አካል ሲነቅፉ ተደምጠዋል።
አቡነ ማትያስ በንግግራቸው በኦሮሚያ፣ በቤንሻንጉል፣ በሸዋ ሮቢት እና በሌሎችም የሀገሪቱ ክፍሎች ችግር እንዳለ ይታወቃል ያሉ ሲሆን፣ ነገር ግን የትግራይን ያህል እንዳልሆነና በትግራይ የተፈጠረውን ‹‹እጅግ የከፋ፣ እጅግ ጭካኔ የተሞላበት የአረመኔያዊነት ሥራ›› ብለውታል፡፡
«የትግራይን ህዝብ ለማጥፋት ይፈልጋሉ፤ የትግራይን ዘር ለማጥፋት ለምን እንደፈለጉ ግልፅ አይደለም» በማለት የሚናገሩት አቡነ ማቲያስ በትግራይ ክልል አሁንም ድረስ ግድያው እየተካሄደ መሆኑን ገልጸው፣ በክልሉ ሲቪሊያን ተገድለው ወደ ገደል እንደተጣሉ፣ ቤት ለቤት እየተዞረ ወጣቶች እንደሚገደሉ፣ እንዲሁም እርሳቸው ‹‹ከሁሉም የከፋ እና የነውር ነውር›› ሲሉ የገለጹት በሴቶች ላይ ከፍተኛ የመደፈር እና ሌሎችም ለመናገር የሚዘገንኑ ጥፋቶች እንደተፈጸሙ ዘርዝረዋል፡፡
አቡኑ ጨምረውም የትግራይ ሕዝብ ‹‹ንብረቱም፣ መብቱም፣ ሕይወቱም ተገፏል›› በማለት እየተደረገ ነው በማለት በአሁኑ ወቅት ‹‹ገበሬዎች እርሻ እንዳያርሱ›› መከልከላቸውንም ተናግረዋል፡፡
አቡነ ማትያስ በንግግራቸው በክልሉ በአብያተ ክርስትያናት ላይ ተፈጽሟል ስላሉት ውድመትም አንስተዋል፡፡ በዚህም በደብረ ዳሞ፣ በአክሱም እና በዋልድባ በአብተ ክርስትያናት እና በመነኮሳት ላይ ጥቃት እንደደረሰ ገልጸዋል፡፡
የዋልድባ መነኮሳት እድሜ ልካቸውን ከኖሩበት ገዳም በዘራቸው እየተመረጡ ተባረዋል ያሉት አቡነ ማትያስ፣ አቅም ያላቸው ሲያመልጡ አቅመ ደካሞቹ ግን ከመንገድ መቅረታቸውንም አስረድተዋል፡፡
‹‹እግዚአብሔር የራሱ ዳኝነት አለው›› ሲሉ የተደመጡት ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ ለዓለም መንግሥታት እና ለዓለም አብያተ ክርስቲያናት የተለየ የድጋፍ የጠየቁ ሲሆን፣ በግል ያሉበትን ሁኔታ በተመለከተ ‹‹ሁላችሁም ወገኖቻችን ማወቅ ያለባችሁ፣ እዚህ ያለውን የኔን ችግር የማውቀው እኔ ነኝ›› በማለት ዝርዝሩን ከመናገር ግን ተቆጥበዋል፡፡