Thursday, November 28, 2024
spot_img

ምርጫ ቦርድ የኦነግን ጠቅላላ ጉባኤ እና ጉባኤው ያሳለፈውን ውሳኔ እንዲቀበል ፍርድ ቤቱ መወሰኑ ተነገረ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ሚያዝያ 29፣ 2013 ― የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በእነ አራርሶ ቢቂላ የሚመራው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) መጋቢት 4፣ 2013 ያደረገውን የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ እና በስብሰባው ያሳለፈውን ውሳኔ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንዲቀበለው መወሰኑ ተነግሯል።

በወቅቱ ጉባዔ የኦነግ ምክትል ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡት አቶ ቀጄላ መርዳሳ ነግረውኛሎ ብሎ አል ዐይን እንገዘገበው በቦርዱ እና በፓርቲው መካከል የነበረው ክርክር ዛሬ እልባት አግኝቷል፡፡

ኦነግ በውስጥ ችግሩ ምክንያት ጠቅላላ ጉባዔ ሳያካሂድ በመቆየቱ “የምርጫና የዕጩ ምዝገባ ጊዜ አልፎብናል” በማለት ቦርዱ ችግሩን ግምት ውስጥ በማስገባት የምልክት መረጣና የዕጩ ተወዳዳሪዎች ምዝገባ እንዲያደርግ እንዲፈቅድለትና ጠቅላላ ጉባኤውንም እንዲያጸድቅለት ቦርዱን በደብዳቤ ጠይቆ ነበር።

ቦርዱም የቀረቡትን ሰነዶች በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 እና በፓርቲው ህገ ደንብ መሰረት መርምሮ ባሳለፈው ውሳኔ፤ አዲስ የተመረጡትን የኦነግ አመራሮች እና የተካሔደውን ጉባኤ እንደማይቀበል አስታውቋል፡፡

ውሳኔውን በማስመልከት መጋቢት 19፣ 2013 ባወጣው መግለጫ “የተከናወነው ጠቅላላ ጉባኤ ተቀባይነት የለውም”በማለት ወስኖ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ኦነግ መጋቢት 4፣ 2013 ያደረገው ጠቅላላ ጉባኤና ያሳለፈው ውሳኔ ተቀባይነት እንዲያገኝ ይግባኝ ብሎ እንደነበርም አይዘነጋም፡፡

ሆኖም ቦርዱ ይግባኙን አለመቀበሉን ተከትሎ ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ተወስዶ ነበር፡፡

ጉዳዩን የተመለከተው የከፍተኛ ፍርድ ቤትም ይግባኝ ባይ መጋቢት 4፣ 2013 ያደረገው ጠቅላላ ጉባኤና ያሳለፈው ውሳኔ ተቀባይነት አለው ብሏል፡፡

እንደ ምክትል ሊቀመንበሩ ቀጄላ መርዳሳ ገለጻ፣ ቦርዱ ኦነግ ያደረገውን ጠቅላላ ጉባዔ እና የተወሰነውን ውሳኔ እንዲያስፈጽም ፍርድ ቤቱ ወስኗል።

ይህንኑ ውሳኔ ተከትሎም “ጠባብ ቢሆንም በምርጫው ለመሳተፍ የሚያስችል የተወሰነ ዕድል አለን” ሲሉ አቶ ቀጀላ ገልጸዋል፡፡

በውሳኔው ላይ ምርጫ ቦርድ እስካሁን ያለው ነገር የለም።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img