አምባ ዲጂታል፤ ረቡዕ ሚያዝያ 4፣ 2015 – ዓለም አቀፎቹ የፋይናንስ ተቋማት አይኤምኤፍ እና ዓለም ባንክ ኢትዮጵያ አሁንም የብርን የመግዛት አቅም እንድታዳክም የያዙትን አቋም አጠናክረው እንደገፉበት ተነግሯል፡፡ ተቋማቱ በኢትዮጵያ ያለውን የሁለትዮሽ የውጭ ምንዛሬ ገበያ እንዳይቀጥል ለማድረግ የሚያስችል መፍትሔ ለማግኘት በዚህ ሳምንት ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር ስብሰባ ሊቀመጡ መሆናቸውም ነው የተሰማው፡፡
የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እና የገንዘብ ተቋማቱ ሰዎች ስብሰባ በዚሁ ሳምንት መካሄድ በጀመረው የሁለቱ ተቋማት ዓመታዊ የስፕሪንግ ጉባዔ ጎን ለጎን እንደሚካሄድ የተገለጸ ሲሆን፣ በዚሁ ስብሰባ ላይ ለመካፈል የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምሕረቱና የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴን ጨምሮ የኢትዮጵያ ልዑክ ጉባዔውን ለመካፈል በዋሽንግተን ይገኛል፡፡
ይህ ስብሰባ የሚደረገው የኤይኤምኤፍ የባለሞያዎች ቡድን ለሳምንታት በኢትዮጵያ ያደረገውን ቆይታ አጠናቆ ከተመለሰ በኋላ ነው፡፡ የባለሞያዎች ቡድኑ ከኢትዮጵያ ቆይታው በኋላ ባወጣው አጭር መግለጫ፣ የአገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ቁጥር ሁለትን ለመደገፍ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ስምምነት ላይ መድረሱን አስታውቋል፡፡ በረቂቅ ደረጃ ያለው ሁለተኛው የአገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም ዶክመንት የምንዛሬ ገበያው ቀስ በቀስ መከፈቱ (Liberalize መደረግ) እንዳለበት ይጠቁማል፡፡
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ የዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት ዴቪ ማልያስና የአይኤምኤፍ ዋና ዳይሬክተር ባደረጉት የጋራ ውይይት፣ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች ካሉበት ውስብስብ ችግሮች እንዴት መውጣት እንደሚችሉ ከጉባዔው መፍትሔ ሊገኝ ይችላል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡
በዚሁ ውይይት ዴቪድ ማልያስ ‹‹በኢትዮጵያ ያለው የሁለትዮሽ የምንዛሪ ገበያ ትልቅ ማነቆ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ሕጋዊው የምንዛሪ ገበያ ጥቂቶችን ብቻ ነው የሚያገለግለው፡፡ ሕገ ወጥ የሆነው የትይዩ ገበያ ደግሞ በጣም ውድ ስለሆነ እሱም ጥቂቶችን ያገለግላል፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ምንዛሪ ገበያ ውጤታማ ሊሆን አልቻለም፡፡ ይህን ችግር ለመፍታት በዚህ ሳምንት በጠረጴዛ ዙሪያ እንሰባሰባለን›› ብለዋል፡፡ ፕሬዘዳንቱ በኢትዮጵያ ካለው 120 ሚሊዮን ሕዝብ አብዛኛው በሁለትዮሽ ገበያ ሥርዓት ምክንያት እየተጎዳ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ሪፖርተር ጋዜጣ ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ ሁለት ተቋማት በኢትዮጵያ ሕጋዊውን የምንዛሬ ገበያና የትይዩ ገበያን አንድ ለማድረግ የብርን የመግዛት አቅም አሁን ካለበት ቢያንስ በእጥፍ በማውረድ የጥቁር ገበያው አሁን ካለበት እኩል ማድረግ ግዴታ መሆኑን ሲወተውቱ ነበር፡፡ የዕዳ ሽግሽግን በተመለከተም ተጨባጭ ውሳኔ ከዚህ ጉባዔ እንደሚጠበቅ ኃላፊዎቹ ጠቁመዋል፡፡ ሁሉም አበዳሪዎች ከተበዳሪዎች ጋር ለመጀመርያ ጊዜ በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ እንደሚመክሩ ተነግሯል፡፡ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ በአይኤምኤፍ አማካሪነት ሀብታም አገሮችና ሌሎች አበዳሪዎች ሊያደርጉ ከተስማሙት የታዳጊ አገሮች ዕዳ ሽግሽግ ተጠቃሚ ለመሆን የሁለትዮሽ ምንዛሪ ገበያውን አንድ ማድረግ እንዳለባት እንደ ቅድመ ሁኔታ እንደተጠየቀ ዘገባው አመልክቷል፡፡
ጋዜጣው ያናገራቸው የምጣኔ ሐብት አማካሪ በበኩላቸው ብሔራዊ ባንክ ውሳኔውን ከተቀበለ ባለፉት ዓመታት በቁጥቁጥ ሳያወርድ የነበረውን የብር የመግዛት አቅም በቅርቡ ያንሸራትታል ብለዋል፡፡ ነገር ግን ይህ ውሳኔ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዲመጣ ማድረግ ቢችልም፣ የጎንዮሽ ጉዳቱ ግን የገቢ ምርቶችን ማስወደድና በኢትዮጵያ ያለውን የዋጋ መናር ማባባስ ነው ሲሉ አክለዋል፡፡