- በክልል ላዩ ኃይሎች ጉዳይ መግለጫ ያወጣው ኢዜማ፤ ውሳኔውን በመደገፍ ሂደቱን ‹‹ፈንጅ የማምከን ያህል ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚፈልግ›› ነው ብሎታል
አምባ ዲጂታል፤ ዐርብ መጋቢት 29፣ 2015 – የፌዴራል መንግሥት የክልል ልዩ ኃይልን ትጥቅ በማስፈታት ሥራ በአማራ ክልል ‹‹ሒደቱን የሚያውኩ ተግባራት›› ታይተዋል ሲል ያስታወቀው የክልል ልዩ ኃይሎች ወደ ተለያዩ የፀጥታ መዋቅሮች እንዲገቡ የሚያስችላቸው ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንደጀመረ በገለጸበት መግለጫው ነው፡፡
በመንግሥት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት በኩል ትላንት ሐሙስ መጋቢት 28፣ 2015 በወጣው መግለጫ፤ መንግሥት የሀገሪቱን ሉአላዊነትና የግዛት አንድነት መጠበቅ የሚያስችል አንድ ጠንካራ የተማከለ ሠራዊት ለመገንባት አቅጣጫ ማስቀመጡን ጠቅሷል፡፡
በዚሁ አግባብ የክልል ልዩ ኃይሎችን በተለያዩ የፀጥታ መዋቅሮች የማካተቱ ውሳኔና ትግበራ በጥናት ላይ ተመሥርቶ የሚከናወን መሆኑን ያመለከተው መግለጫው፤ ሂደቱም በሁሉም ክልሎች የሚተገበር መሆኑንም ያትታል፡፡ መንግስት ሥራውን በጥናት፣ በእቅድ እና በጥንቃቄ እየመራው እንደሚገኝ በመግለጫው ላይ ሠፍሯል፡፡
ሆኖም መንግስት በአማራ ክልል በሚገኙ ‹‹የተወነሱ ልዩ ኃይሎች››፣ በአንድ በኩል ‹‹የመልሶ ማደራጀት ሥራውንና ዓላማውን በአግባቡ ባለመረዳት››፤ በሌላ በኩል ‹‹የጥፋት አጀንዳ አራጋቢዎች ሆን ብለው በሚነዙት የሐሰት ወሬ በመጠለፍ›› ሂደቱን የሚያውኩ ተግባራት መታየታቸውን ገልጧል፡፡ የመንግሥት መግለጫ ይነዛሉ ካላቸው ሐሰተኛ ወሬዎች መካከል የመልሶ ማደራጀቱ በአማራ ክልል ብቻ የሚካሄድ መሆኑንና ሕወሓት ትጥቅ ሳይፈታ እንዴት የክልሉ ልዩ ኃይል ትጥቅ ይፈታል የሚለው እንደሚገኝበት ጠቁሟል፡፡
ሥራው በሁሉም ክልሎች በተመሳሳይ ጊዜ እየተካሄደ የሚገኝ ነው ያለው መንግሥት፤ የሕወሓት ትጥቅ የመፍታት ሂደትም በፕሪቶሪያ በተፈረመው ስምምነት መሠረት ‹‹ያለማወላወል የሚፈጸም እንጂ ከሌላ አገራዊ አቅድ ጋር የሚጣረስም የሚቀናጅም አይደለም ሲል አብራርቷል፡፡
መንግሥት በመግለጫው ማሳረጊያ የክልል ልዩ ኃይሎችን እንደገና የማደራጀቱ ሥራ ለዘላቂ የሃገር ጥቅምና ደህንነት የወሰንኩት በመሆኑ ሃላፊነቱንም በከፍተኛ ጥንቃቄ እወጣዋለሁ ብሏል፡፡
መንግሥት የክልል ልዩ ኃይሎችን ትጥቅ ለማስፈታት እያካሄደ ያለውን እንቅስቃሴ ተከትሎ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች መግለጫዎችን እያወጡ ይገኛሉ፡፡ በትላንትናው እለት መግለጫ ያወጣው አብን መንግሥት የአማራ ልዩ ኃይል ትጥቅ እንዲፈታ ያሳለፈውን ውሳኔ በአፋጣኝ እንዲቀለብስ ያሳሰበ ሲሆን፣ በዛሬው እለት መግለጫ ያወጣው ኢዜማ በበኩሉ የክልል ልዩ ኃይሎችን ወደ ፌደራልና የክልል ህጋዊ የፀጥታ መዋቅር ውስጥ የማስገባት በጎ ጅምር አላስፈላጊ ውዥንብር ፈጥሮ ሌላ ሀገራዊ አደጋ እንዳይጋብዝ ጥንቃቄ እንደሚፈልግ አስታውቋል፡፡
ኢዜማ በመግለጫው የመንግሥትን ውሳኔ ‹‹ከመዘግየቱ በስተቀር ተገቢነቱ ላይ ጥያቄ ሊነሳበት አይገባም›› ብሎታል፡፡ ‹‹ከሕጋዊ አሠራር ውጪ›› ተቋቁመዋል ያላቸውን የክልል ልዩ ኃይሎች በፌደራል መንግሥት የፀጥታ ዕዝ ሥር እንዲገቡ መደረጉ ‹‹ተገቢ እና ልክ›› እንደሆነ ገልጧል፡፡
ነገር ግን እነዚህን የክልል ልዩ ኃይሎች ወደ ህጋዊ የፀጥታ መዋቅር ሥር የማስገባት ሂደት አተገባበር ‹‹ፈንጅ የማምከን ያህል ከፍተኛ ጥንቃቄ›› የሚፈልግ ነው ሲል በአጽንኦት አሳስቧል፡፡
ፓርቲው በመግለጫው አያይዞም በቅርቡ ከአሸባሪነት መዝገብ እንዲፋቅ የተደረገው የህወሓት ቡድን በሚቆጣጠራቸው መገናኛ ብዙኃን በኩል በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል ሥር ያሉ አካባቢዎችን ስለማስመለስ እንደሚሠራ በስፋት እያስተጋባ ባለበት በዚህ ወቅት፤ ይህን ውሳኔ በጥድፊያ እና በድብቅ ተግባራዊ ለማድረግ መሞከር አደገኛ ውጤት እንደሚያመጣ የፌደራል መንግሥት ሊገነዘበው እንደሚገባም በማስታወስ፤ ህወሓት የታጠቃቸውን መሣሪያዎች መፍታቱ በግልጽ ባልታወቀበት ሁኔታ የትግራይ አዋሳኝ ክልሎች ዳግም የመወረር ስጋት ቢያድረባቸው የሚያስወቅስ እንዳልሆነ ጠቁሟል፡፡
በመሆኑም የውሳኔውን አፈጻጸም ቅደም ተከተል በተመለከተ ጥንቃቄ እንዲደረግ የጠቆመው ኢዜማ፤ የተጀመረው በጎ እርምጃ አላስፈላጊ ውጥንቅጥ ፈጥሮ ሌላ ሀገራዊ አደጋ እንዳይጋብዝ በማለት ሊደረጉ የሚገባቸውን ጥንቃቄዎች ዘርዝሯል፡፡ ኢዜማ ከዘረዘራቸው ቅድመ ጥንቃቄዎች መካከል መንግሥት የክልል ልዩ ኃይሎችን ወደ ህጋዊ የፀጥታ መዋቅር ውስጥ ለማካተት የወሰነውን ውሳኔ ‹‹እስካመነበት እና ሌላ ድብቅ የፖለቲካ ሴራ ከሌለ በስተቀር›› ውሳኔውን በድብቅ ለማስፈጸም የሚያደርገው እንቅስቃሴ አላስፈላጊ ውዥንብር እንዲሁም ግጭት ከመፍጠር ያለፈ ፋይዳ እንደሌለው በመገንዘብ ልዩ ኃይሉን ወደ መደበኛነት ለመቀየር የሚከተለውን ፍኖተ ካርታ ደረጃ በደረጃ አካሄዱን ለህዝብ በተደጋጋሚና ግልፅ በሆነ መልኩ በተለያዩ ቋንቋዎች ማብራሪያ እንዲሰጥ ጠይቋል፡፡ በተጨማሪም የሁሉንም ክልሎች ልዩ ኃይሎች ወደ ህጋዊ የጸጥታ ተቋማት ውስጥ ማካተት የሚኖረውን ሀገራዊ ጠቀሜታ እና አፈጻጸም በተመለከተ ከኹሉም የክልል መንግሥታት ኃላፊዎች እና የፀጥታ ተቋማት ጋር ተነጋግሮ መግባባት ላይ መድረስ በቅድሚያ ሊኾን እንደሚገባ ያስታወሰው ኢዜማ፤ የጉዳዩን ሀገራዊ ፋይዳ ለሚመለከታቸው የሀገራችን የፖለቲካ ልሂቃን ከማስረዳት ጀምሮ፤ ይህን ውሳኔ ሰበብ በማድረግ ሊሸረቡ ከሚችሉ ፖለቲካዊ ደባዎች መታቀብም በከፍተኛ ደረጃ ሊታሰብበት ይገባል ብሏል፡፡ ከአንዳንድ የፖለቲካ ተዋንያን እየተሰማ እንዳለው “የአንዱን ክልል ልዩ ኃይል አፍርሶ ሌላኛውን በድብቅ የማጠናከር ሴራ” እንዳይኖር ማድረግ እንደሚገባም ውሳኔውን ለሚያስፈጽሙ የሀገር መከላከያ እና የፌደራል ፖሊስ አዛዦች በጥብቅ አሳስቧል፡፡
ፓርቲው በመግለጫው ማሳረጊያ ለፖለቲካ ተዋንያን በሙሉ ባስተላለፈው መልዕክት የክልል ልዩ ኃይሎችን የፈጠረው መዋቅራዊ አሠራር ጭምር በጥልቀት እንዲታሰብበት አሳስቧል፡፡ በዚህም በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ክልሎች፤ መገናኛ ብዙኀን፤ የንግድ ተቋማት፤ ባንኮች፤ የስፖርት ቡድኖች፤ የሙያ ማኅበራት፤ የምሑራን ስብስብ እና ሌሎችም መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማት በአንድ ዘውግ ስም ተቋቁመው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተባብሮ ወደ ልማት ሳይኾን ተከፋፍሎ ወደ እርስ በእርስ ግጭት እንዲገባ እንደሚያደርጉት ለአፍታም መዘንጋት እንደሌለበት ነው ያመለከተው፡፡ ይህ የዘውግ ክፍፍል ወደ ሰማያዊዎቹ የሃይማኖት ተቋማት ጭምር ገብቶ ችግር ፈጥሯል ያለው ፓርቲው፤ አንድ ተቋም ለአንድ ዘውግ ጥቅም ብቻ ሲቋቋም በአንድ ሀገር ሕዝብ መካከል “እኛና እነሱ” የሚል ክፍፍል እና አሉታዊ ፉክክር በመፍጠር የግጭት መንስኤ እንደሚኾን መገንዘብ እንደሚያስፈልግና የክልል ልዩ ኃይሎችም የዚሁ የዘውግ ፖለቲካ ነፀብራቅ እንደኾኑ መታወቅ አለበት ብሏል፡፡ ስለዚህም፤ የዚህ ሕጋዊ እና መወቅራዊ የዘውግ ክፍፍል መነሻ ምክንያት የኾነው የዘውግ ፖለቲካ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ከኢትዮጵያ ሊወገድ ይገባል ብሏል፡፡