Tuesday, December 3, 2024
spot_img

የአይኤምኤፍ ባለሥልጣናት ኢትዮጵያ ሊደረግላት ስለሚችለው ድጋፍ ቴክኒካዊ ሥራ ለማከናወን አዲስ አበባ እንደሚገኙ ተዘገበ

አምባ ዲጂታል፤ ረቡዕ መጋቢት 20፣ 2015 – የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ባለሥልጣናት ኢትዮጵያ ሊደረግላት ስለሚችለው ድጋፍ አስፈላጊውን ቴክኒካዊ ሥራ ለማከናወን አዲ አበባ እንደሚገኙ የዘገበው ብሉምበርግ ነው፡፡

ለአስር ቀናት ገደማ አዲስ አበባ ይቆያሉ የተባሉት የተቋሙ ባለሥልጣናት ወደ ኢትዮጵያ ያቀኑት በሰሜን የተካሄደው ጦርነት አብቅቶ በግጭት እና በድርቅ የተጎዳውን ምጣኔ ሃብቷን እንዲያገግም ለማድረግ ጥረት በተጀመረችበት ወቅት ነው።

ኢትዮጵያ ለአይኤምኤፍ የገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግላት መጠየቋ የተነገረ ሲሆን፣ የአይኤምኤፍ ባለሥልጣናት በዚህ ሳምንት አዲስ አበባ ውስጥ የሚያደርጉት ቴክኒካዊ ውይይት፣ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እና በተቋሙ መካከል ሰብአዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ችግሮችን ለማሻሻል የተደረገ ንግግር ተከታይ መሆኑን የተቋሙ ቃል አቀባይ ገልጸዋል።

ቃል አቀባዩ ለሬውተርስ የዜና ወኪል ‹‹ሊሰጥ የሚችለው ድጋፍ አገሪቱ ለምታካሂደው አገር በቀል የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ እና ምጣኔ ሀብቷን በማረጋጋት ለሰብአዊ ድጋፍ፣ ለሥራ ፈጠራ እና ለድህነት ቅነሳ የሚውል ይሆናል›› ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ እና በዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም መካከል ሲካሄድ የነበረው የድጋፍ፣ የብድር ስረዛ እና ሽግሽግ ንግግር በከፊል በትግራይ ሲካሄድ ከነበረው ጦርነት ጋር ተያይዞ ምላሽ ሳያገኝ ቆይቶ ነበር።

ብሉምበርግ እንዳለው ኢትዮጵያ ጦርነቱ ያስከተለውን ውድመት መልሶ ለመገንባት እና የገጠማትን የውጭ ምንዛሪ እጥረት በመሸፈን አስፈላጊ ለሆኑ የገቢ ምርቶች ክፍያ ለመፈጸም ድጋፍ ያስፈልጋታል።

በጦርነቱ እና በዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች ምክንያት ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ችግር የገጠማት ሲሆን፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከፍተኛ የሸቀጦች ዋጋ ጭማሪ ከመመዝገቡ በላይ እጥረትም ተከስቷል።

በኢትዮጵያ በትግራይ ጦርነት የደረሰውን ውድመት መልሶ ለመገንባት 20 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፍልግ የመንግሥት ባለሥልጣናት በቅርቡ ተናግረዋል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img