Sunday, September 22, 2024
spot_img

የሕወሓት ሰዎች ከፌዴራል መንግስት ጋር በሥልጣን መጋራት ዙርያ ለመደራደር መዘጋጀታቸውን ገለጹ

  • ሕወሓት በጊዜያዊ አስተዳደሩ የፕሬዝዳንቱን ቦታ ለመያዝ ማቀዱ ተነግሯል

አምባ ዲጂታል፤ ቅዳሜ የካቲት 18 2015 – ከፌዴራል መንግሥት ጋር ለሁለት ዓመታት በጦርነት ውስጥ ቆይቶ በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተደረገው የዘላቂ ተኩስ ማቆም ስምምነት በኋላ ሠላም ያወረደው ሕወሓት፤ በትግራይ ክልል ከሚቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር አስቀድሞ በሥልጣን መጋራት ዙርያ ከመንግሥት ጋር ለመደራደር መዘጋጀቱን ገልጧል፡፡

በፕሪቶሪያው ስምምነት የሕወሓት ዋንኛ ተደራዳሪ የነበሩት አቶ ጌታቸው ረዳ፤ ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደተናገሩት ከፌዴራል መንግሥት ከስምምነት ሳይደርስ ምንም ማድረግ እንደማይቻል በመጠቆም፤ ለመደራደር እየተዘጋጀን ነው ብለዋል፡፡ አቶ ጌታቸው በእነርሱ በኩል ይህ አቋም ቢያዝም የፌዴራል መንግሥት ግን እየተዘጋጀ ይሁን ወይም አይሁን አላረጋገጥኩም ነው ያሉት፡፡

በመንግሥት እና ሕወሓት የፕሪቶሪያ ስምምነት በምርጫ ቦርድ በኩል ምርጫ ተደርጎ የትግራይ ክልል የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ተወካዮች እስከሚመሠረት ድረስ ጊዜያዊ አስተዳደር እንደሚቋቋም ሠፍሯል፡፡

በሚቋቋመው የትግራይ ጊዜያዊ አስተደዳር የፌዴራል መንግሥቱን የሚመራው ብልጽግና፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እና ክልሉን ሲያስተዳድር የቆየው ሕወሓት ድርሻ ይኖራቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከፓርቲዎቹ መካከል ሕወሓት ከመንግሥት ጋር ጦርነት መግጠሙን ተከትሎ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት እንደተፈረጀና በምርጫ ቦርድም ከፓርቲነት እንደተሰረዘ ይታወቃል፡፡ የሕወሓት ተወካዮ ጌታቸው ረዳ ወደ ፊት ለመራመድ ሕወሓትን ከሽብር ዝርዝር ጉዳይ በመንግሥት መፍትሔ የሚፈልግ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡  

በሌላ በኩል ሪፖርተር ጋዜጣ የሕወሓት ሰዎች ከመንግሥት ጋር በሚያደርጉት ድርድር የክልሉን ፕሬዝዳንት ቦታ ለራሳቸው ወስደው፣ ምክትል ቦታዎችን ለብልጽግና እና ለተቃዋሚዎች ለመተው ማቀዳቸውን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸውን ሰዎች ጠቅሶ ዘግቧል፡፡

በትግራይ ክልል የሚቋቋመውን ጊዜያዊ አስተዳደር ለማቋቋም በሚደረገው ሂደት ከሰሞኑ በሕወሓት የተዘጋጀ ሰነድ ለውይይት መቅረቡ ሲገለጽ፤ በአንጻሩ የክልሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሕወሓት ላይ ያላቸውን ቅሬታ እያሰሙ ይገኛሉ፡፡

የፌዴራል መንግሥት በበኩሉ በትግራይ ለሚቋቋመው የጊዜያዊ አስተደደር የመከላከያ ሚኒስቴር እና የደህንነት መስሪያ ቤት ሰዎችን ያካተተ ኮሚቴ ያቋቋመ ቢሆንም፤ በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የሚቋቋምበት ትክክለኛ ጊዜ አልተቆረጠም፡፡ የሕወሓት አመራሩ ጌታቸው ረዳም ጊዜያዊ አስተዳደር ለማቋቋም አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ነገር ግን የፌዴራል መንግሥቱ የሚያቀርቡትን ምክረ ሐሳብ ይቀበላቸው አይቀበላቸው የሚታወቀው ከድርድሩ በኋላ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ አቶ ጌታቸው ስለ ምክረ ሐሳቡ እና ድርድር መታቀዱን ቢገልጹም፤ የድርድሩን ፍሬ ነገር ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img