Monday, October 7, 2024
spot_img

መጪው ምርጫ ዓለም አቀፍ መመዘኛዎችን አያሟላም ላሉት አምስቱ የአሜሪካ ሴናተሮች አምባሳደር ፍጹም አረጋ ምላሽ ሰጡ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ሚያዝያ 28፣ 2013 ― በመጪው ወር የሚካሄደው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ አሁን ባለበት ሁኔታ ነጻ፣ ሚዛናዊ እና ግልጽ ሆኖ ዓለም አቀፍ መመዘኛዎች አያሟላም በማለት በጆ ባይደን አስተዳደር የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው ለተሾሙት አምባሳደር ጆፍሪ ፌልትማን ደብዳቤ ለጻፉት አምስት የአሜሪካ ሴናተሮች በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

አምባሳደር ፍጹም በደብዳቤያቸው ምርጫውን አስፈጻሚው ቦርድ ገለልተኛ መሆኑን እንዲሁም መንግሥት ምርጫው ዲሞክራሲያዊ እና ተዓማኒነት ያለው እንዲሆን ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አምባሳደሩ ለሴናተሮቹ በጻፉት ምላሽ በቀጣዩ ምርጫ ለመሳተፍ 47 ፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከ8 ሺሕ በላይ እጩዎች መመዝገባቸውን አስታውሰው፣ ከምርጫ ጋር ተያይዘው የሚነሱ አለመግባባቶችን የፍትሕ አካሉ በገለልተኛነት ይመለከታቸዋል ብለዋል።

ዓለም አቀፍ የምርጫ ታዛቢዎችም ምርጫውን እንዲታዘቡ ጥሪ እንደቀረበላቸውም የገለጹት አምባሳደር ፍጹም፣ በየትኛውም አገር የሚካሄድ ምርጫ ፍጹም ነው ተብሎ እንደማይጠበቅና ስድስተኛው ሃገራዊ ምርጫ ‹‹ኢትዮጵያን ወደ መድበለ ፓርቲ ሥርዓት ያሸጋግራታል ብለን እናምናለን›› ሲሉ አስፍረዋል፡፡

አምባሳደሩ በደብዳቤያቸው አክለውም ሴናተሮቹ ባነሷቸው ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

ከቀናት በፊት ደብዳቤውን ለፌልትማን የጻፉት ሴናተሮቹ ቤንጃሚን ኤል ካርዲን፣ ቲም ኬይን፣ ጃኪ ሮስን፣ ኮርይ ኤ ቡከር እና ኤድዋርድ ጄ ማርኬይ ነበሩ፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img