Sunday, September 22, 2024
spot_img

የትግራይን ሕዝብ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት በቀጣይ የማረጋገጥ ዕቅድ መያዛቸውን የሕወሓት ቃል አቀባይ ገለጹ

  • ተኩስ ቢቆምም ‹‹ጦርነቱ አለቀ ማለት አይደለም›› ብለዋል

አምባ ዲጂታል፤ ማክሰኞ ኅዳር 06፣ 2015 ― ከፌዴራል መንግሥት ጋር በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በተፈረመው የሠላም ስምምነት ሕወሓትን ወክለው የፈረሙት ቃል አቀባዩ አቶ ጌታቸው ረዳ፤ የትግራይን ሕዝብ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት በፖለቲካ ውይይት የማረጋገጥ ዕቅድ መያዛቸውን ገልጸዋል፡፡

አቶ ጌታቸው ይህን ያሉት በጦርነቱ በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በረሃብና በግድያ ሞተው፤ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶችም የፆታዊ ጥቃት ሰለባ ሆነውና የተለያዩ ጥሰቶችም ተፈጽመው ከዚህ ሁሉ በኋላ ‹‹ትግራይ ምን አተረፈች›› በሚል ከቢቢሲ ለተሰነዘረላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ነው፡፡

በምላሻቸው ‹‹ከጦርነት የሚገኝ ትርፍ የለም›› ያሉት ጌታቸው፤ ‹‹ህልውናችንን ለማረጋገጥ የሚያስችል አቋም ይዘን ትርፍ ሳይሆን ቢያንስ እንካሳለን ብለን እናምናለን›› ሲሉ ከድርድሩ በኋላ ለማግኘት ያለሙትን ገልጸዋል፡፡

የዜና ተቋሙ ‹‹የትግራይ ካሳ ምን ይሆናል›› በሚል ላስከተለው ጥያቄ የሕወሓት ዋና ተደራዳሪው ሲመልሱ፤ ‹‹ሕዝቡ ምኞቱን እና ፍላጎቱን፣ ወይ አገር ይሁን ወይ የሆነው ይሁን እኔ መወሰን ስለማችል፥ ሙሉ በሙሉ የሚያረጋግጥበት ሁኔታ መፍጠር ነው ነው ካሳው›› ብለዋል፡፡ አያይዘውም ‹‹ይህን ለማድረግ በሰላማዊ መንገድ ወይም በጦርነት የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን፤ የትግራይ ሕዝብ ይህን ከማድረግ ወደ ኋላ አይልም›› በማለት አክለዋል፡፡

ጨምረውም ከፌዴራል መንግሥት ጋር በነበረው ድርድር የተቀበሉት ‹‹የተኩስ አቁም›› መሆኑን በመጥቀስ፤ ‹‹ተኩስ ከቆመ በኋላ የፖለቲካ ውይይት ይቀጥላል። በፖለቲካ ውይይት የትግራይን ሕዝብ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ካላረጋገጥኩኝ ተኩስ ለማቆም ስለወሰንኩ ብቻ የሚቀበለኝ ሰው ይኖራል›› ወይ ሲሉ ጥያቄውን በጥያቄ መልሰዋል፡፡ አቶ ጌታቸው ‹‹የትግራይ ሕዝብ እና የትግራይ ሠራዊት እኔ እንደፈለግኩ የምነዳው አይደለም›› ሲሉም ነው የተናገሩት፡፡

ፌዴራል መንግሥትም ይሁን ዓለም አቀፍ መንግሥታትም ይሁኑ ማንም ይሁን የትግራይን ሕዝብ ፍላጎት ከማሟላት ውጪ አማራጭ ያለው አይመስለኝም›› ያሉት ጌታቸው፤ ‹‹ዋናው ተኩሱ ይቁም፣ የትግራይ ሕዝብ እርዳታ ይቅረብለት፣ አገልግሎት ያግኝ፣ በፖለቲካዊ ውይይት በሰላማዊ መንገድ የሚፈታ ነገር ካለ እናያለን፤ መፍታት ካልተቻለ ትጥቅ ይፍታ ስላልኩት የሚፈታ ሠራዊት የለም›› ብለዋል፡፡

ከዚሁ ጋር በተገናኘ ጦርነቱ አብቅቷል ወይ የተባሉት ጌታቸው፤ እንዳላበቃ በመግለጽ፤ ‹‹ተኩስ አቁመናል፤ ጦርነቱ አለቀ ማለት አይደለም›› ሲሉ መልሰዋል፡፡

ለድፍን ሁለት ዓመታት በጦርነት ውስጥ የቆዩት የፌዴራል መንግስት እና ሕወሓት ጥቅምት 23፣ 2015 በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መፈራረማቸው ይታወቃል፡፡ በተፈረመው የሰላም ስምምነት መሰረት የመንግስትና የሕወሓት የጦር አዛዦች በተኩስ አቁም አፈፃፀም፣ በጦር ስራዊት አሰፋፈር እንዲሁም በትጥቅ መፍታት ጉዳይ ላይ በተመሳሳይ ባለፈው ቅዳሜ ስምምነቱን ለመተግበር ቁርጠኝነታቸውን በፊርማ አረጋግጠዋል፡፡

በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረትም የፌደራል መንግሥት መቀሌን ተረክቦ በከተማው ውስጥ እና ዙሪያ ሁሉንም አይነት የጦር መሣሪያ ያስፈታል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ አሁን ያለው የሕወሓት መዋቅር ፈርሶ የፌደራል መንግሥት የሚመራው የጊዜያዊ አስተዳደር እንደሚቋቋምም ሠፍሯል፡፡ በሚዋቀረው ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥም የትግራይን ሕዝብ የሚወክል አካል ይሳተፋል፤ በትግራይ የሚመሰረተው ጊዜያዊ አስተዳደር በሁሉም የትግራይ አካባቢዎች የማኅበራዊ አገልግሎቶች በፍጥነት እንዲጀመሩ ሁኔታዎች ያመቻቻል፤ ተግባራዊነታቸውን እንደሚያረጋግጥም ስምምነቱ ያመለክታል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img