አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ሚያዝያ 28፣ 2013 ― የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብደላ ሐምዶክ አገራቸው ሱዳን በሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ከስምምነት ላይ ካልተደረሰ በኢትዮጵያ እጅ ስለምትወድቅ ስምምነቱ የግድ አስፈላጊ መሆኑን ከሲኤንኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል፡፡
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሆነ ስምምነት ላይ ካልተደረሰ ኢትዮጵያ በግድቡ ጉዳይ የፈለገችውን እንድታደርግ እድል ይሰጣታል፡፡
የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር በድርድሩ ጉዳይ የአፍሪካ ኅብረትን በተመለከተ በኢትዮጵያ በኩል የሚነሳውን ‹‹ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ›› በሚለው አቋም ዙሪያም የተናገሩ ሲሆን፣ ይህን አቋም ቀድማ ያመጣችው አገራቸው እንደሆነች በመግለጽ አሁንም ቢሆን ኅብረቱ በቶሎ ከስምምነት እንዲደረስ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡
በሌላ በኩል ከኢትዮጵያ ጋር ስለገቡበት የድንበር ውዝግብ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብደላ ሐምዶክ፣ አገራቱ ተስማምተውበታል ያሉትን የ1902 ስምምነት ጠቅሰው በዚሁ መሠረት ችግሩን ለመፍታት የጋራ ኮሚቴ ተቋቁሟል በማለት አሁንም ለንግግር በሯ ዝግ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡