Sunday, October 6, 2024
spot_img

የቀድሞው ሜቴክ የሕዳሴው ግድብ ደን ምንጣሮ ላይ የተሳተፉ 38 ማኅበራትን ባለእዳ አድርጓል ተባለ

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ሚያዝያ 27፣ 2013 ― በቀድሞው የኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) በ2006 የታላቁ ሕዳሴ ግደብ ደን ምንጣሮ ሥራ ለሰሩ 160 ጥቃቅንና አነስተኛ ማኅበራት መክፈል ያለበትን ገንዘብ ሳይከፍል፣ በተጭበረበረ ሰነድ 38 ማኅበራትን ባለ ዕዳ እንዲሆኑ ማድረጉ ተነግሯል፡፡

እንደ አዲስ ማለዳ ጋዜጣ ዘገባ ከሆነ ሜቴክ በ2006 ከ160 ማኅበራት ጋር ውል ገብቶ ያስመነጠረውን 56 ሺሕ ሄክታር ደን ክፍያ በሁለት ዙር የከፈለ ሲሆን፣ ደን ምንጣሮው ካጠናቀቁ በኋላ ሦስተኛ ዙር ክፍያ እንዳልተከፈላቸው ማኅበራቱ ተናግረዋል።

ሜቴክ በወቅቱ ለ160 ማኅበራት መክፍል የሚገባውን 340 ሚሊዮን ብር እንዳልከፈለ የማኅበራቱ ተወካይ አቶ እሱባለው ተካልኝ ገልጸዋል።

ማኅበራቱ 340 ሚሊዮን ብር ሊከፈላቸው ሲገባ፣ ሜቴክ የገባውን ውል ብቻውን በማፍረስ 38 ማኅበራትን የ31 ሚሊዮን ብር ባለ እዳ አድርጓል ሲሉ ነው አቶ እሱባለው ጉዳዩን ያስረዱት።

ማኅበራቱ የሰሩበት ክፍያ የተከለከሉበት ምክንያት ምንጣሮው የተካሄደበት ቦታ መጠን ልኬት ሲሆን፣ በሰሩት ሥራ በሁለት ዙር ከተከፈላቸው በኋላ የመጨረሻው ከፍያ በሚከፈልበት ጊዜ በኮንትራት ሰጪውና በኮንትራት ተቀባዮቹ መካከል ውዝግብ ያስነሳው የዚሁ የመለኪያ ዘዴው ጉዳይ ነበር።

የመለኪያ ዘዴው ውዝግብም ሜቴክ ‹‹በጂፒኤስ ይለካል›› ሲል ማህበራቱ ደግሞ፣ ‹‹ቦታው ወጣ ገባ የበዛበት ስለሆነ፣ በሜትር ይለካልን›› የሚል ሀሳብ ማቅረባቸው ነበር።

ሁለቱ መለኪያዎች ልዩነት ይኖራቸው እንደሆን ለማረጋገጥ ሲባልም፣ ለናሙና የተወሰደ ቦታ በሜትርና በጂፒኤስ ተለካ፣ በሜትር ተለክቶ 12 ሄክታር የሆነው ቦታ፣ በጂፒኤስ ሲለካ ከ6 ሄክታር በታች እንደሆነ አቶ እሱባለው አስታውሰዋል።

በዚህም ትክክለኛው መለኪያ ሜትር መሆኑ በኹለቱም ወገኖች ስለታመነበት፣ ሜትር ገመድ እየተጣለ ይለካ ጀመር፣ በዚህም ልኬት ሜቴክ በሦስት የተለያዩ ምዕራፎች ለማኅበራቱ ክፍያ የፈጸመበት ማስረጃ በማኅበራቱ እጅ ይገኛል።

ይሁን እንጅ ማኅበራቱ 340 ሚሊዮን ብር ሊከፈለን ሲገባ ጂፒኤስ ከግማሽ በላይ ልኬቱን እንደሚቀንስ ተረጋግጦ በሜትር እንዲለካ ስምምነት ላይ ተደርሶ፣ በዚሁ መሠረት ሲከፈላቸው ቆይቶ ‹‹ልኬቱ ተጭበርብሯል›› በሚል ሰበብ ሜቴክ ሥራውን የሰሩ ማኅበራትን ሳያሳትፍ በጂፒኤስ ለክቶ አዲስ የልኬት ውጤትና የሂሳብ መጠን እንዳቀረበ ቅሬታቸውን ገልፀዋል።

አዲስ በቀረበው ልኬትና የሂሳብ መጠን 160 ማኅበራት የሚከፈላቸው 340 ሚሊዮን ብር ቀርቶ 38 ማኅበራት 31 ሚሊዮን ብር ተመላሽ እንድናደርግ ተጠይቀናል ብለዋል እሱባለው። ሜቴክ ለ160 ማኅበራት ሦስተኛ ዙር ክፍያ 340 ሚሊዮን ብር ለመክፈል ለማኅበራቱ የክፍያ ሰርተፍኬት ተስጥቶ እንደነበር እሱባለው ጠቁመዋል።

ማኅበራቱ በ2007 ፍርድ ቤት ክስ አቅርበው ፍርድ ቤቱ መለኪያውን በተመለከተ፣ በተከሳሽ(ሜቴክ) ጠቋሚነት፣ ለኢትዮጲያ ካርታ ሥራዎች ድርጅት፣ ‹‹ከጂፒኤስና ከሜትር የትኛው የተሻለ ይህንን መሬት ይለካል?›› ብሎ እንዳቀረበ እሱባለው ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ ካርታ ሥራዎች ድርጅት፣ ‹‹እንደዚህ ዓይነት ወጣ ገባ የበዛበትን ቦታ ለመለካት ሜትር እንደሚመረጥ፣ ጂፒኤስ ግን፣ የእንደዚህ ዓይነቱን ቦታ የቆዳ ስፋት በትክክል እንደማይሰጥ የፃፈው ደብዳቤ ቀርቦ በወቅቱ የተሰየሙት ዳኛ “ፍርድ ቤቱ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል›› ማለታቸውን አሱባለው የፍርድ ሂደቱን አስታውሰዋል።

ጉዳዩ በማኅበራቱና በአባላቱ ህልውና ላይ ብዙ ምስቅልቅል ሁኔታዎችን አስከትሏል፤ ንብረታቸውን አስይዘው ለሥራ ማስኬጃ የተበደሩትን መክፈል አቅቷቸው ንብረታቸው ተይዟል፤ ለሠራተኞቻቸው የሚከፍሉት አጥተው ክስ የተመሠረተባቸው፣ ድርጅቶቻቸው የተዘጉ፣ የታሠሩ፣ አገር ለቀው የጠፉ፣ ቤተሰቦቻቸው የተበተኑ እንዳሉ አቶ እሱባለው አስረድተዋል።

ጋዜጣው የቀድሞው ሜቴክ የአሁኑ ኢትዮ – ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሞላልኝ ከሳቴብርሃን አነጋግሬ ደርጅቱ በብዙ የሙስና ሥራዎች ተዘፍቆ የቆየ መሆኑን በማስታወስ ጉዳዩ የቀድሞ ድርጅቱ አመራሮች መሆኑን ገልጸውልኛል ብሏል።

ድርጅቱ በቀድሞው አመራሮቹ ምክንያት በሙስና ከአገሪቱ ተቋማት ቀዳሚ እንደነበር የጠቆሙት አቶ ሞላልኝ አሁን ላይ ድርጅቱ በለውጥ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img