Sunday, September 22, 2024
spot_img

መንግሥት ሕወሓትን ‹‹የትግራይ መንግሥት›› ብሎ መጥራት የአገሪቱን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ የሚጥል ነው አለ

አምባ ዲጂታል፤ ዐርብ መስከረም 27 2015 ― የፌዴራሉ መንግሥት የኢትዮጵያ ወዳጆች እና የአገሪቱን ሉዓላዊነት፣ የግዛት አንድነትና ሕገ መንግሥት እናከብራለን የሚሉ ሕወሓትን ‹‹የትግራይ መንግሥት›› ብሎ ከመጥራት እንዲታቀቡ አሳስቧል፡፡

ዛሬ መስከረም 27፣ 2015 በመረጃ ማጣሪያ ገጽ በተላለፈው መልእክት፤ መንግሥት ከዚህ በተጨማሪ ሕወሓትን ለመጥራት አግባብነት የላቸውም ያላቸውን ሌሎች አገላለጾች ዘርዝሯል፡፡

ከእነዚህ መካከል የሕወሓት ሰዎች በደብዳቤያቸው የሚጠቀሙበት ‹‹የትግራይ የውጪ አገልግሎት›› የሚለው በተመሳሳይ የአገሪቱን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ከተባሉት ውስጥ ተጠቅሷል፡፡  

በተጨማሪም መንግሥት የኢትዮጵያ ወዳጆች እና አጋሮች ከሰሞኑ ይካሄዳል በተባለው ድርድር ተደራዳሪዎቹ ፍጹም ልዩነት ያላቸው ወገኖች መሆናቸውን እንዳይዘነጉ አሳስቧል፡፡ መንግሥት እንዳይዘነጋ ያለው ጉዳይ ድርድሩ አንድ በሕጋዊ መንገድ ‹‹በተመረጠ መንግሥት እና በታጣቂው ሕወሓት›› መካከል የሚደረግ ስለመሆኑ ነው፡፡

ከዚሁ ጋር በተገናኘ ‹‹የትግራይ አስተዳደር›› እና ‹‹የትግራይ ክልላዊ መንግሥት›› የሚለውን አገላለጽ በተመሳሳይ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን የገለጸው መንግሥት፤ በትግራይ ክልል በሕገ መንግሥቱ መሠረት የተመረጠ አካል ሥልጣን ላይ እንደሌለ ሊታወቅ ይገባል ብሏል፡፡

በተጨማሪም ድርድሩን በፌዴራል መንግሥት እና በትግራይ ክልል የሚደረግ ነው ማለትም ተቀባይነት የሌለው ከመሆኑ ባሻገር ብሔራዊ ሉዓላዊነትን የሚጥስ ስለመሆኑም አስፍሯል፡፡

በሚቀጥለው ጥቅምት ወር መጨረሻ ሁለት ዓመት የሚደፍነውን የፌዴራል መንግሥት እና ሕወሓት ጦርነት በሰላም ለመቋጨት ነገ ቅዳሜ መስከረም 28፣ 2015 የሚጀምር ሽምግልና በደቡብ አፍሪካ ለማካሄድ የአፍሪካ ኅብረት ቀጠሮ ይዟል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img